በመዲናዋ የተከፈቱት የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት የመኖር ተስፋችንን አለምልመዋል – የምገባ ማዕከሉ ተጠቃሚዎች

You are currently viewing በመዲናዋ የተከፈቱት የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት የመኖር ተስፋችንን አለምልመዋል – የምገባ ማዕከሉ ተጠቃሚዎች

AMN – ግንቦት 11 / 2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በበጎ አድራጊ ግለሰቦችና ተቋማት ትብብር የሚንቀሳቀሱት “የተስፋ ብርሃን” የምገባ ማዕከላት፣ በከተማዋ ለሚገኙ በርካታ አቅመ-ደካሞች፣ የጎዳና ተዳዳሪዎች፤ ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸዉ አረጋውያን የምግብ ዋስትና እየሆኑ መምጣታቸውን ተጠቃሚዎች ገለጹ።

በቦሌ ሚካኤል አካባቢ የተከፈተዉ 26ኛው የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል፣ በቀን ከ300 በላይ ለሆኑ ዜጎች ንጹሕና ትኩስ የዕለት ጉርስ በማቅረብ ማኅበራዊ ሸክምንና ውጣ-ውረድን በእጅጉ እያቃለለ ይገኛል።

የምገባ ማዕከሉ የብዙዎችን ተስፋ ከማለምለም ባለፈ፣ ዜጎች ሰብአዊ ክብራቸው ተጠብቆ የዕለት ምግባቸውን እንዲያገኙ እያደረገ መሆኑን ተጠቃሚዎች ተናግረዋል፡፡

ከማዕከሉ ተጠቃሚዎች መካከል አቶ ዮርዳኖስ ግርማ ፤ ቀደም ሲል ከወጣትነት ዕድሜያቸው ጀምሮ በከባድ መኪና አሽከርካሪነትና በኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ በመሰማራት ሀገራቸውን ለረጅም ዓመታት ማገልገላቸዉን ይናገራሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት በጡረታ ላይ የሚገኙት እኚህ አዛውንት፣ በገጠማቸው የጤና እክል ምክንያት የሰውን እጅ ለመጠባበቅ ተገድደው እንደነበር ያስታውሳሉ። አሁን ግን ከማዕከሉ በቀን አንድ ጊዜ ትኩስ ምግብ እያገኙ መሆናቸዉንና የምገባ አገልግሎቱ የመኖር ተስፋን እንደፈጠረላቸዉ ገልጸዋል፡፡

ሌሎች በማዕከሉ የምገባ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑ እናቶችና አቅመ-ደካማ ነዋሪዎች በበኩላቸዉ ፣ ማዕከሉ ከመከፈቱ በፊት ለቀናት ምግብ የማግኘት ዕድል እንዳልነበራቸዉ አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ግን የከተማ አስተዳደሩ ባመቻቸላቸው የምገባ አገልግሎት በተደራጀው የኩፖን አሠራር መሠረት በክብር ተስተናግደው የዕለት ምግባቸውን ማግኘት መቻላቸውን ገልጸዋል።

ከተደረገላቸው የዕለት ጉርስ ድጋፍ በተጨማሪ፣ ማዕከሉ ከተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ጋር በማስተሳሰር የልብስ ማጠብ የሥራ ዕድሎችን እያመቻቸላቸው እንደሚገኝም ተጠቃሚዎቹ ተናግረዋል፡፡

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review