AMN የካቲት 23/2018
የዓድዋ ድል ምስጢሩ የዓላማ ጽናት እና የሀገር ፍቅር መሆኑን የኢትዮጵያ ጥንታዊት ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ተናገሩ፡፡
130ኛው የዓድዋ ድል በዓል ፒያሳ በሚገኘዉ የዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተከበረ ይገኛል፡፡
በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ጥንታዊት ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ኢትዮጵያ ከ130 ዓመታት በፊት የተፈጸመባትን ወረራ እና ግፍ በሕዝባዊ መራራ ተጋድሎ በአሸናፊነት ነጻነቷን አጽንታ የዘለቀች የጀግኖች ምድር ነች ብለዋል፡፡
የዚህ አስደማሚና ዓለምን ያነጋገረ ታሪካዊ ድል ምስጢሩ የዓላማ ጽናት እና የሀገር ፍቅር መሆኑን ገልጸው አሁንም ለጥፋት የሚታትሩ ኃይሎች ታሪካችንን ወደ ኋላ መለስ ብለው በማስታወስ ራሳቸውን ከታሪካዊ ስህተትና አስከፊ ጥፋት እንዲታደጉ ምክራቸውን ለግሠዋል።
ኢትዮጵያን ለማወክ የሚመጣን ማንኛውም የጥፋት ኃይልን ግን የአርበኞች ምድር የሆነች ኢትዮጵያ ከቶም ዝም ብላ አትመለከትም ብለዋል በመልዕክታቸው፡፡
ትናንት በዓድዋ ላይ የተጎናጸፍነውን አስደናቂ ድል ዛሬም በሌሎች ተግባሮቻችን ላይ ድሎችን በማስፋት አዲሱ ትውልድ የአያቶቹን አደራ ተቀብሎ ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ከፍታ እንዲያሻግር ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ በትውልዱ እጅ ላይ ነው ያሉት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን የተቀበላችሁትን ሰንደቅ ዓላማ ጠብቁ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በትዝታ መንግስቱ