AMN – ሰኔ 24/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ መንግሥት እያከናወናቸው ያሉት የቱሪዝም እና የቅርስ እድሳት ስራዎች ታሪካዊ ቅርሶችን ለመጠበቅ፣ ለማስዋብ እና ለትውልድ ለማሻገር ያለሙ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሀገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ በሚመለከት በሰጡት ቃለ ምልልስ ፣ በመንግሥት የቅርስ እድሳት ፕሮጀክቶች ዙሪያ “ቅርሶቹ አይጠፉም ወይ?” በሚል ለሚነሳው ስጋትና ትችት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ይህ አይነቱ ትችት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልምምድ ደካማ ከመሆኑ የተነሳ ስለ ሁሉም ነገር ተቃውሞ ከሚያንጸባርቁ አካላት የሚመነጭ መሆኑን ገልጸዋል።
“ቅርስ እኛ የምናስመልስ፣ የምንጠብቅ ነን እንጂ የምናፈርስ አይደለንም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰሩት ስራዎች መንግሥት የቅርስ ጠባቂ እና አሻጋሪ መሆኑን በተግባር ያሳዩ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በጎንደር ፋሲል ግንብ፣ በላሊበላ፣ በጅማ አባ ጅፋር ቤተ-መንግስት፣ በሐረር ጀጎል እና በአዲስ አበባ ብሄራዊ ቤተ-መንግስት የተከናወኑትን የእድሳት እና የጥገና ስራዎችን ለአብነት አንስተዋል።
በተለይም ብሔራዊ ቤተመንግሥት ከእድሳቱ በፊት ምቹ ያልሆነ እና አስከፊ ገጽታ እንደነበረው አስታውሰው አሁን ግን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሚጎበኙት ስፍራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ የፋሲል ግንብ እድሳትም ህዝቡም ሆነ የውጭ ጎብኚዎች የሚኮሩበት መሆኑን አክለው ገልጸዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘመናት ተዘርፈው ወደ ውጭ ሀገራት የተወሰዱ ከ35 በላይ ታሪካዊ ቅርሶችን ማስመለሷን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
ከነዚህም ውስጥ በሌላ ሀገር የሚገኘው የአፄ ኃይለስላሴ የዙፋን መቀመጫ ወንበር በቅርቡ ወደ ሀገር ቤት እንደሚመለስ አብስረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መንግሥት በቱሪዝም ዘርፍ የሚሰራቸው ስራዎች ሁሉንም ሃይማኖቶች እና አካባቢዎች በእኩልነት የሚያዩ እና የኢትዮጵያን አጠቃላይ ገጽታ የሚያሳዩ በልዩ ትኩረት የሚሰሩ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በትዝታ መንግስቱ