AMN- የካቲት 25/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን ውበት ለመጠበቅና የዲጂታል ማስታወቂያ አጠቃቀምን ስታንዳርድ ለማስከበር ባደረገው ዘመቻ፣ ባለፉት 15 ቀናት ውስጥ ብቻ ከ4 ሺህ 500 በላይ ህገ-ወጥ የውጭ ማስታወቂያዎችን ማንሳቱን አስታውቋል።
በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ በተከናወነው ህግ የማስከበር ሥራ ከህገ-ወጥ ማስታወቂያ ባለቤቶች ላይ ከ1.4 ሚሊየን ብር በላይ የቅጣት ገቢ መሰብሰቡን የከተማዋ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን የውጭ ማስታወቂያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ግርማቸው ጌታነህ ገልጸዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፣ ባለስልጣኑ የከተማዋን ገጽታ የሚያበላሹ ማስታወቂያዎችን ለመቆጣጠር በሰፊው እየሰራ ይገኛል።
በዚህም በ2017 በጀት ዓመት ከ60 ሺህ በላይ ህገ-ወጥ የውጭ ማስታወቂያዎች ላይ እርምጃ የተወሰደ ሲሆን፣ በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ከ29 ሺህ 470 በላይ ማስታወቂያዎች በህግ አግባብ እንዲመሩ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም ጥራትና ደረጃቸውን የጠበቁ የዲጂታል ማስታወቂያዎች ፈቃድ አሰጣጥ ስራ በተሟላ ሁኔታ ተፈጻሚ እየሆነ ይገኛል ብልዋል።
የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ጽሕፈት ቤት የውጭ ማስታወቂያ ቡድን መሪ አቶ አደራ ጅሩ በበኩላቸው፣ ማስታወቂያዎቹ በስታንዳርድ ደረጃ ቢሰቀሉም ይዘታቸው እንደ ጫትና ማሳጅ ያሉ ያልተፈቀዱ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ፣ ከህንጻው ጋር የማይጣጣሙ፣ እንዲሁም የከተማዋን የቀለም ስምምነት የማይከተሉ በመሆናቸው እርምጃ ሊወሰድባቸው መቻሉን አብራርተዋል።
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ጽሕፈት ቤት የውጭ ማስታወቂያ ቡድን መሪ ሰላማዊት ዝግያለው፣ የማስታወቂያ ሥራ ባህሪው ሰፊ በመሆኑ ህገ-ወጥ ተግባራትን ሙሉ በሙሉ ለማስቆም የህብረተሰቡ ግንዛቤ ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።
በቀጣይ ህብረተሰቡ የተሻለ እውቀት ኖሮት ከህገ-ወጥ አሰራር እንዲርቅ የተጀመሩ የግንዛቤ መፍጠር ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
የከተማ አስተዳደሩ አዲስ አበባ የጀመረችውን የውበትና የጽዳት ጉዞ ለማሳካት መሰል የቁጥጥር ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተመልክቷል።
በበረከት ጌታቸው