AMN- የካቲት 27/2018 ዓ.ም
መመለሻ ቀናቸው አልፎ ለአምስት አስርት ዓመታት የጠፉትና ዳግም አይገኙም ተብለው ተስፋ የተቆረጠባቸው ሁለት ታሪካዊ መጻሕፍት፣ በድንገት ካሉበት ተገኝተው ወደ ቤተ-መጻሕፍቱ ተመልሰዋል።
በእንግሊዝ ሊድስ ማዕከላዊ ቤተ-መጻሕፍት እ.አ.አ. በ1976 መመለስ የነበረባቸው እነዚህ የጂኦሎጂ መጻሕፍት፣ ከ50 ዓመታት በኋላ በአንድ ያገለገሉ ዕቃዎች መሸጫ ሱቅ ውስጥ በድንገት መገኘታቸው ብዙዎችን አስገርሟል።
የሊድስ ከተማ ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ፣ መጻሕፍቱ የተገኙት ከመነሻቸው 60 ማይል ገደማ ርቆ በሚገኘው ምስራቅ ዮርክሻየር ቤቨርሊ ውስጥ ነው።
በዚያ በሚገኝ አንድ ያገለገሉ ዕቃዎች መሸጫ ሱቅ ውስጥ የሚሰሩ ሠራተኞች፣ ለሱቁ ከተበረከቱ መዋጮዎች መካከል የሊድስ ማዕከላዊ ቤተ-መጻሕፍት ማህተም ያለባቸውን መጻሕፍት ሲመለከቱ ለሚመለከተው አካል ጥቆማ ሰጥተዋል።
መጻሕፍቱም በሬቨረንድ ዊልያም ቡክላንድ የተጻፉት “Geology and Mineralogy” የተሰኙት መጻሕፍት ቁጥር 1 እና 2 ናቸው።
እነዚህ የማጣቀሻ መጻሕፍት የታተሙት እ.ኤ.አ በ1836 ሲሆን፣ ከቤተ-መጻሕፍቱ በውሰት የወጡት ግን ከግማሽ ክፍለ ዘመን በፊት ነበር።
በውስጣቸው ባለው መረጃ መሠረት የመመለሻ ቀናቸው እ.ኤ.አ በመጋቢት 1976 የነበረ ቢሆንም፣ ሳይመለሱ ለ50 ዓመታት ቆይተዋል።
የሊድስ ማዕከላዊ ቤተ-መጻሕፍት ባለሙያ የሆኑት ሳሊ ሂውዝ፣ መጻሕፍቱ ወደ ቤተ-መጻሕፍቱ በመመለሳቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
ከነዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ እነዚህ ውብ መጻሕፍት ባልተጠበቀ ቦታ መገኘታቸው ድንገተኛ ነገር የሆነባቸው ባለሙያዋ፣ ግማሽ ክፍለ ዘመን ዘግይተውም ቢሆን ወደ ቤታቸው በመመለሳቸው ታላቅ እርካታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።
ሳሊ ሂውዝ አክለውም መጻሕፍቱን ማን እንደወሰዳቸውና ለምን ለዚህ ሁሉ ዘመን እንደቆዩ ፈጽሞ ላናውቅ እንችላለን ብለዋል፡፡
መጻሕፍቱ ከተጻፉ ከ180 ዓመታት በላይ ቢቆጠሩም፣ አሁንም ድረስ የሰዎችን ቀልብ መሳባቸው፣ የሬቨረንድ ቡክላንድ ሳይንሳዊ ምልከታዎች ምን ያህል ጥልቅና ሳቢ እንደነበሩ ማሳያ ናቸው ማለታቸውን ዩ ፒ አይ ዘግቧል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ