ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የጎበኙት የ“ናሲኦል” ዋሻ በዋሻ ተመራማሪው ናስር አሕመድ ስም መሰየሙን ያውቃሉ?

You are currently viewing ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የጎበኙት የ“ናሲኦል” ዋሻ በዋሻ ተመራማሪው ናስር አሕመድ ስም መሰየሙን ያውቃሉ?

AMN – መጋቢት 01/2018

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምስራቅ ሐረርጌ ዞን በመገኘት “ናሲኦል” የተባለውን ዋሻ ጎብኝተዋል።

ይህ ዋሻ በታዋቂው የዋሻ አሳሽ ናስር አሕመድ ስም መሰየሙን ያውቃሉ?

“ናሲኦል” የተባለው ዋሻ ሳይንቲስት ናስር አሕመድ ካከናወናቸው ረጅም የጥናት ሥራዎች መካከል አንዱ ሲሆን፣ በዋሻ ጥናት ሳይንስ ላይ ላበረከተው ምርምርና አስተዋጽኦ ስሙ ለዋሻው ተሰጥቷል።

ተመራማሪው እንደገለጹት፣ የዋሻ ጥናት አድካሚ ሥራ ቢሆንም ትልቅ የቱሪዝም እና የታሪክ ሀብትን የያዘ ነው።

ተመራማሪዉ ናስር አሕመድ የምስራቅ ሐረርጌ ዞን የኮምቦልቻ ወረዳ ተወላጅ ሲሆኑ፣ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው፣ በአፍሪካ ደግሞ ሁለተኛው የዋሻ ተመራማሪ በመሆን ይታወቃሉ።

እስከ አሁን ድረስ 334 የተፈጥሮ ዋሻዎችን የመረመሩ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ በ200ዎቹ ላይ መጽሐፍ መጻፋቸውን ከኤም ኤን ዲጂታል ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

የዋሻዉ ስሙ ‘ናስር’ ከሚለው ‘ናሲ’ ተወስዶ ‘ኦል’ (በአፋን ኦሮሞ የበላይ ወይም ከፍ ያለ ማለት ነው) የሚል ተጨምሮበት ‘ናሲኦል’ ተብሎ መሰየሙን ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስፍራዉ ያደረጉት ጉብኝት የተፈጥሮ እና የቱሪዝም ሀብቶችን በማስተዋወቅና በመጠበቅ ላይ የመንግስትን ትኩረት የሚያሳይ ነው።

በተጨማሪም፣ እነዚህ ዋሻዎች ስለ አየር ንብረት ለውጥ፣ ስለ መሬት ታሪክ እና ስለ ግብርና ልማት ትልቅ ሳይንሳዊ መረጃ ሊሰጡ እንደሚችሉ ተመራማሪው ገልጸዋል።

ለዚህም ቀጣይነት ያለው ጥናት መደረግ እንዳለበት ተመልክቷል።

ሳይንቲስት ናሲር አሕመድ ከኤም ኤን ዲጂታል ጋር በነበራቸው ቆይታ “እነዚህ ዋሻዎች የሀገራችን ትልቅ ሀብት በመሆናቸው፣ የሚቀጥለው ትውልድ ይህንን ጥናት እንዲቀጥልበት የመንግስት ድጋፍ ያስፈልጋል” ብለዋል።

አሳሹ ናሲር አሕመድ አክለውም፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር የናሲኦልን ዋሻ በመጎብኘታቸው የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታ ገልጸዋል።

ይህ ጉብኝት ለረጅም ጊዜ ለሰሩት የምርምር ሥራ ትልቅ እውቅና እንደሆነም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው ወቅት “ኢትዮጵያ ተዝቆ የማያልቅ ሀብት እንዳላት የናሲኦል ዋሻ ህያው ምስክር ነው” ማለታቸው ይታወሳል።

በደራርቱ ተሬሳ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review