ጠቅላይ ምክር ቤቱ ለሆስፒታሎች የሚውል ከ101 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የመድኃኒትና ሕክምና ግብዓቶች አበረከተ

You are currently viewing ጠቅላይ ምክር ቤቱ ለሆስፒታሎች የሚውል ከ101 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የመድኃኒትና ሕክምና ግብዓቶች አበረከተ

AMN መጋቢት 1/2018

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ለአምስት የመንግስት ሆስፒታሎች የሚውል ከ101 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የመድኃኒትና የሕክምና ግብዓቶች ድጋፍ አበርክቷል።

በኢትዮጵያ ሙስሊሞች የልማት ኤጀንሲ አማካኝነት የተበረከተው ድጋፍ በዑስታዝ አቡበከር አህመድ አስተባባሪነት ከሙስሊም ኤይድ አሜሪካ የተገኘ መሆኑ ተገልጿል።

በድጋፍ ርክክብ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ፣ የምክር ቤቱ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚደንት ሸይኽ አብዱልከሪም ሸይኽ በድረዲን፣ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሰሃረላ አብዱላሂና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

ድጋፎቹም ለአቦምሳ ጠቅላላ ሆስፒታል፣ ኮምቦልቻ ጠቅላላ ሆስፒታል፣ ጭናክሰን የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፣ ጉንችሬ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልና ቋንጤ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የሚውሉ ናቸው።

በዚሁ ወቅት የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ እንደገለጹት፤ ምክር ቤቱ ኃይማኖታዊ ግዴታን በመወጣት በዜጎች ማህበራዊና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በንቃት እየተሳተፈ ነው።

ለአምስቱ ሆስፒታሎች የተበረከተው የመድኃኒትና የሕክምና ግብዓቶች ድጋፍም የረመዳን ወር የመተሳሰብና የመደጋገፍ መሆኑን በተግባር እንደሚያረጋግጥ ገልጸዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሰሃረላ አብዱላሂ በበኩላቸው፤ ለሆስፒታሎቹ የተበረከተው የመድኃኒትና የሕክምና ግብዓቶች ድጋፍ ለጤና ተቋማት ተጨማሪ አቅም መሆኑን በመግለጽ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review