የህገ ወጡ የህወሓት አመራሮች የፈጸሟቸው ስሌት አልባ ውሳኔዎች የትግራይን ህዝብ ለከፍተኛ ችግር ዳርገዋል – የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ

You are currently viewing የህገ ወጡ የህወሓት አመራሮች የፈጸሟቸው ስሌት አልባ ውሳኔዎች የትግራይን ህዝብ ለከፍተኛ ችግር ዳርገዋል – የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ

AMN – ኅዳር 6/2019 ዓ.ም

የህገ ወጡ የህወሓት አመራሮች የፈጸሟቸው ስሌት አልባ ውሳኔዎች የትግራይን ህዝብ ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸዉን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ ገለጹ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ ከኤንቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የግብጽን የረጅም ጊዜ ፖለቲካዊ አቋም፣ የሀገሪቱን የውጭ ጉዳይ ዲፕሎማሲ እና የውስጥ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች አስመልክቶ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አቶ ጌታቸው በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት፣ ግብጽ የህዳሴውን ግድብ እንደ ብቸኛ የህልውና ጉዳይ አድርጋ ለማቅረብ ብትሞክርም፣ ዋናው አጀንዳዋ ግን በአባይ ወንዝ ላይ የነበራትን የሞኖፖል ዕዝ የማስቀጠል ጥረት መሆኑን አንስተዋል።

የግብጽ መሪዎች ከቀድሞ ጀምሮ ኢትዮጵያን ለመጫን እና ግድቡን ለማስተጓጎል የተለያዩ ዓለም አቀፍ ኃይሎችንና ኪራይ ሰብሳቢ አካሄዶችን ቢጠቀሙም፣ ግድቡ ግን ህዝባዊና ራሱን የቻለ አቅም በመገንባት እውን መሆኑን አብራርተዋል።

በሌላ በኩል፣ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከታሪካዊ ትረካዎችና አባባሎች ባለፈ በሀገር ውስጥ የሚከናወኑ የተግባር ስራዎችን፣ የኢኮኖሚ ለውጦችን እና ተቋማዊ አቅሞችን በብቃት ማስተባበር እንደሚገባው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በሚያደርጓቸው ውይይቶች የሀገሪቱን እውነተኛ ገጽታ፣ ሁለንተናዊ እውነታዎች እና የፖሊሲ አቅጣጫዎች በሰለጠነና በእውቀት ላይ በተመሰረተ መንገድ የማቅረቡ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

በተጨማሪም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተከሰቱ ግጭቶች እና የህገወጡ የህወሓት አመራሮች የወሰዷቸው የተሳሳቱ ስትራቴጂዎች በህዝቡ ላይ ያደረሱትን ከባድ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አቶ ጌታቸው አንስተዋል።

የህገወጡ የህወሓት አመራሮች የፈጸሟቸው ስሌት አልባ ውሳኔዎች የትግራይን ህዝብ ለከፍተኛ ችግር የዳረጉ መሆኑን ጠቅሰው፣ የትኛውንም የፖለቲካ ወይም የልዩነት ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ እና ከግጭት በጸዳ መልኩ መፍታት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review