AMN ኅዳር 6/2019 ዓ.ም
ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሃገር ነች፡፡
የተለያዩ ሃይማኖቶች፤ ቋንቋዎች፤ ባህሎችና ማንነቶች የሚገኙባት የብዝሃነት ተምሳሌት ነች፡፡
ኢትዮጵያዊያን በብሄር፤ በሃይማኖት፤ በቋንቋ፤ በባህልና በማንነት ቢለያዩም እንደ አንድ ህዝብ ግን ለሃገራቸው ሉዓላዊነትና ነጻነት በጋራ ቆመዉ ተፋልመዋል፤ አኩሪ ድሎችንም ተጎናጽፈዋል፡፡
በጽኑ የወንድማማችነት መሰረት ላይ የቆሙት የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ተሰባስበዉ በጋራና በአብሮነት ከመኖር አልፈዉ በርካታ የልማት ጸጋዎችንም ለማጣጣም ችለዋል፡፡
በይቻላል መንፈስ የዉስጥና የዉጭ ጫናዎችን ተቋቁመዉ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በጋራ ገንብተዉ ያጠናቃቁት የኢትዮጵያ ብሄር፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፤ ህገወጥ በሆነ መንገድ ያጡትን የባህር በር ህጋዊ መሆነ መንገድ ለማግኘት በጋራ በመትጋት ለይ ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እነዚህንና መሰል በደም ያተጋመዱ ሕያዉ ታሪካዊ እሴቶች ቢኖሯቸዉም የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ግን ይህንን የብዝሃነት ምሶሶን ለመናድ የተለያዩ የጥፋት ስልቶችን ሲጠቀሙ ቆይተዋል፡፡
እነዚህ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የብሄር፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን የአንድነት ቋጠሮ ለመፍታትና እርስ በርስ ለማጋጨት ከሚጠቀሙባቸዉ የጥፋት ስልቶች መካከል ሃሰተኛና የተዛቡ ትርክቶች ዋንኞቹ ናቸዉ።
አብዛኞቹ ሃሰተኛ ትርክቶች የኢትዮጵያን ታሪክ፤ ባህልና ማንነት አንድ ወጥ በመሆነ መልኩ ለማስቀመጥ ከሚሞክሩ እና፤ እኛ በፍጹም አንድ አይደለንም፤ ፍጹም ልዩ ነን ከሚሉ እሳቤዎች የሚመነጩ መሆናቸዉን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ፍጹማዊ አንድነትን መሰረት ያደረገዉ ትርክት ብዝሃነትን ለመቀበል ከመቸገሩም በላይ ሌላ ማንነትን በሃይል እስከመጫን የሚደርስ ሲሆን ፤ በልዩነት ላይ የተመሰረተዉ ትርክት ደግሞ ለብሄር ማንነቶች ሰፊ ቦታ በመስጠት ፤ ሃገራዊ አንድነት በአካባቢያዊ ማንነት እንዲዋጥ የሚፈልግ እሳቤ ነዉ፡፡
ሃገራችን ኢትዮጵያም ላለፉት በርካታ አመታት ፍጹም አንድ ነን እና ፍጹም አንድ አይደለንም በሚሉ፤ በአብሮነት መቆምና መታረቅ በማይችሉ ይልቁንም ለመጠፋፋት በሚሞክሩ ዋልታ ረገጥ እሳቤዎች ምክንያት ስትፈተን ኖራለች፡፡

እነዚህ ጽንፈኛ፤ ዘረኛና ዋልታ ረገጥ እሳቤዎች የሃገሪቱን ሰላምና ደህንነት ከመፈታትን አልፈዉ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች መጠቀሚያ እስከመሆን ደርሰዋል።
የሃገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶችም ይህንኑ ክፍተት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በተለይ ብሄርና ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ወንድማማች ህዝቦችን ደም ለማቃባት እና ኢትዮጵያን ለማፍረስ በርካታ ሙከራዎችን ሲያደርጉ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ያለፉት መንግስታዊ ሥርዓቶችም እነዚህን ጽንፈኛ፤ ዘረኛና ዋልታ ረገጥ እሳቤዎችን ከመግራትና ከማዉገዝ ይልቅ ለስልጣን ማቆያነት ሲጠቀሙበት እንደነበር ምሁራን ያስረዳሉ፡፡
ይሁን እንጂ ሃገራዊ ለዉጡን ተከትሎ ከመደመር እሳቤ የመነጨዉ ገዢ ትርክት ጽንፈኛ፤ ዘረኛና ዋልታ ረገጥ እሳቤዎችን ለማረቅና ለማረም ከሚያደርገዉ ብርቱ ጥረት ጎን ለጎን እንደ አድዋ ድል ያሉ የትናንት የጋራ ታሪኮችን መሰረት ያደረጉ አስተሳሳሪ ትርክቶችን በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡
ህብረብሄራዊ አንድነትን መሰረት ያደረገዉ ገዢ ትርክት የኢትዮጵያዊያንን የብሔር፤ የቋንቋ፤ የሃይማኖት፤ ጾታ፤ የአስተሳሰብ፤ የታሪክ ብዝሃነትን እንደ ጌጥና እንደ ጸጋ የሚቀበል ነዉ።
እነዚህን ማንነቶች አስተሳስሮ የያዘ ሃገራዊ አንድነት አለ ብሎ የሚያምን ትርክት በመሆኑ ለብሄረ እና ሃገረ መንግስት ግንባታ ዋንኛ መፍትሄ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡
ዛሬ ላይ እኔ እበልጣለሁ፤ እኔ እሻላለሁ የሚሉ ፤ ሌላዉን ለመቀበል የሚቸገሩ እና ሃገራዊ አንድነትን የሚጻረሩ ኋላ ቀር እሳቤዎች በእኩልነት፤ በአብሮነትና በህብረብሄራዊ አንድነት እሳቤዎች ይገኛሉ።
አግላይና ከፋፋይ እሳቤዎችን ጨምሮ ጽንፈኛ፤ ዘረኛና ዋልታ ረገጥ አመለካከቶች የሰላምና የልማት ጸር መሆናቸዉ በብዙሃኑ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነትን እያገኘ መጥቷል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ