AMN ኅዳር 6/2019 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ግቦችን አስቀምጦ በመሥራት ላይ ይገኛል።
ከእነዚህ ግቦች መካከል በመዲናዋ የሚታየውን የቤት ፍላጎት እና አቅርቦት ችግር መፍታት ቀዳሚው ሲሆን፣ መስተዳድሩ በተለያዩ አማራጮች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን በመገንባት ላይ ይገኛል።
የከተማ አስተዳደሩ ባለፉት አምስት ዓመታት የነዋሪውን የቤት ጥያቄ ለመመለስ በአዲስ የለውጥ እሳቤ 496 ሺህ 971 ቤቶችን በመገንባት ለነዋሪዎች አስተላልፏል።
ከእነዚህ መካከል 26 ሺህ 563 የመንግሥት ቤቶች ለልማት ተነሺዎች፣ እንዲሁም ከ98 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በሁለት ዙር ዕጣ ለቆጣቢዎች የተላለፉ ናቸው።
በአሁኑ ወቅትም በተለያዩ አማራጮች የ179 ሺህ 516 ቤቶች ግንባታ በ24/7 አዲስ የሥራ ባህል እና ዘመኑ የደረሰባቸውን ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም በመፋጠን ላይ ይገኛል።
የከተማ አስተዳደሩ ባለፉት አምስት ዓመታት ለነዋሪዎች ገንብቶ ካስተላለፋቸው እና በአሁኑ ወቅት በመገንባት ላይ ከሚገኙ ከመቶ ሺህ በላይ ቤቶች በተጨማሪ ለረጅም ዓመታት ሳይከፈል የቆየውን የ62 ቢሊዮን ብር የጋራ መኖሪያ ቤት የባንክ ዕዳን መክፈል ችሏል።
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ብቻ 3.18 ቢሊዮን ብር የቦንድ ዕዳ መልሷል።
መስተዳድሩ በአንድ በኩል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን ገንብቶ በማስተላለፍ፤ በሌላ በኩል በከተማው የቤት ግንባታ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የመቶ ሺዎች ቤት ግንባታ በማካሄድ፤ እንዲሁም ካለፈው ሥርዓት የተላለፈና እስካሁን ድረስ ያልተከፈለ ከ65 ቢሊዮን ብር የሚበልጥ የባንክ ዕዳን በመመለስ የነዋሪዎችን መሠረታዊ ጥያቄ ለመቅረፍ በቁርጠኝነት እና በከፍተኛ ትጋት በመሥራት ላይ ይገኛል።
የከተማ አስተዳደሩ የነዋሪዎቹን የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ለመመለስ ካለው ቁርጠኝነት፣ በየጊዜው እያካበተ ከመጣው የቤት ግንባታ የላቀ አፈጻጸም እና ከሚጠቀማቸው የቤት ግንባታ ቴክኖሎጂዎች አንጻር ለረጅም ዓመታት ያልተከፈሉ የባንክ ዕዳዎች እጁን ባይዙት ኖሮ እስካሁን ድረስ ከተላለፉት እና እየተገነቡ ካሉት ቤቶች በተጨማሪ ሌላ መቶ ሺህ ቤቶችን ገንብቶ የማስተላለፍ ዕድል ይኖረው ነበር።
የአዲስ አበባን ብቻ ሳይሆን የሌሎች ከተሞችን እና ክልሎችን የመኖሪያ ቤት ጥያቄ የተረዳው የመደመር መንግሥት በጉባ ብሥራት የ1.5 ሚሊዮን ቤቶች ግንባታን በአዲስ አበባ በይፋ አስጀምሯል።
በአዲስ አበባ ከተማ በ21 ሳይቶች 100 ሺህ ቤቶች በመገንባት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል 50 ሺህ ቤቶች በከተማው በጀት፣ 50 ሺህዎቹ ደግሞ በመንግሥት፣ በግል አጋርነትና በማኅበራት በመገንባት ላይ የሚገኙ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከንቲባ አዳነች አቤቤም በቱሉ ዲምቱ እና በአዲስ ከተማ ቅጠል ተራ በመገኘት የብሎኮቹን የግንባታ ሂደት የጎበኙ ሲሆን ግንባታቸውም በጥሩ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የግንባታው ዋና ዓላማ የሕዝባችንን የመኖሪያ ቤት ጫና ማቃለል እና በመላው አገሪቱ ለሚገኙ ቤተሰቦች የተሻለ የኑሮ ምዕራፍ መክፈት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ከንቲባ አዳነች በበኩላቸው የነዋሪዎች መሠረታዊ ፍላጎትና አንገብጋቢ ጥያቄ የሆነውን የቤት ጫና ማቃለል የልማት ግብ ብቻ ሳይሆን አደራና ኃላፊነት ጭምር በመሆኑ በ24/7 የሥራ ባህል በትጋት እየሠራን እንገኛለን ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ አማራጮች የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለመመለስ ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ ለአቅመ ደካማ ዜጎች እና ለልማት ተነሺዎች ቤት ገንብቶ በማስተላለፍ፣ ማዕድ በማጋራት፣ በምገባ እና በሌሎች ተግባራት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሌት ከቀን በመሥራት ላይ ይገኛል።
የከተማ አስተዳደሩ በመንግሥት፣ በግል አጋርነትና በማኅበራት ከሚያከናውናቸው የቤት ግንባታዎች እና ሌሎች ኢንቨስትመንቶች በተጨማሪ በኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት ባከናወናቸው ሰፊ የልማት ሥራዎች በመዲናዋ የነበረውን የ74 ከመቶ የጎስቋላነት ገጽታ በአስደናቂ ሁኔታ ወደ 30 ከመቶ ዝቅ ማድረጉን ከከተማ አስተዳደሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በወንድማገኝ አሰፋ