ኢትዮጵያ ያሏትን ጸጋዎች አሰባስባ ጠንካራ ሃገራዊ ኢኮኖሚ የምትገነባበትና ሥልጣኔዋን የምታረጋግጥበት ትክክለኛው መንገድ

You are currently viewing ኢትዮጵያ ያሏትን ጸጋዎች አሰባስባ ጠንካራ ሃገራዊ ኢኮኖሚ የምትገነባበትና ሥልጣኔዋን የምታረጋግጥበት ትክክለኛው መንገድ

AMN- ኅዳር 6/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ለእርሻና ለተለያዩ ስራዎች የሚውል ለምና ሰፊ የእርሻ መሬት አላት፡፡ ክረምት ከበጋ የሚፈሱ ወንዞች፤ ምቹ የአየር ሁኔታና የዝናብ ስርጭት፤ አምራች የሰው ሃይል፤ የተለያዩ ማዕድናት፤ የእንስሳት ሃብት እና ሌሎች ጸጋዎች ያላት ሃገር ነች፡፡

የቱሪዝም ሃብቶቿም ቢሆኑ ታይተው የማይጠገቡ፤ ተዳሰው የማያልቁ፤ መንፈስን የሚያድሱ እና ጥልቅ ደስታን የሚፈጥሩ ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ ሃገሪቱ እነዚህን እምቅ ጸጋዎች ማሰባሰብ፤ ወደ ተደራጀ ሃገራዊ አቅም መቀየር እና ቀጣይነት ያለዉ ዉጤት ማስመዝገብ ባለመቻሏ ለትዉልድ መሻገር የሚችል ሃብት መፍጠር አልቻለችም፡፡

በተለይ የግሉ ዘርፍ አዳዲስ ምርቶችንና አገልግሎቶችን ከመፍጠር፤ የፈጠራ አቅምን ከማሳደግ እንዲሁም ምርት የሚመረትበትን አዲስ መንገድ ከማስተዋወቅ ረገድ የላቀ ሚና ቢኖረዉም የሚጠበቅበት ያህል መፈጸም አልቻለም፡፡

የዚህ ችግር ዋንኛዉ መንስኤ ሃገሪቱ ያላትን እምቅ አቅምና ዕሴት አሰባስቦ መጠቀምና ወደ ተደራጀ አቅም ብሎም ወደ አይበገሬ ኢኮኖሚ መቀየር የሚያስችል አስቻይ ስርዓት እና ፖሊሲ አለመኖሩ ነበር፡፡

የመደመር መንግሥት ይህንን ክፍተት ለመሙላት ፖሊሲ ከማዉጣት ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን፤ ማበረታቻዎችን እና እርምጃዎችን በመዉሰድ ላይ ይገኛል፡፡

በተለይ የግሉ ዘርፍ ያሉበትን ችግሮች በመለየት፤ ተቋማትን በማገዝ፤ ሥነ ምህዳሩን ለፈጠራ ምቹ አድርጎ በመቅረጽ እና ስጋቶችን በመጋራት የተበታተነዉን ሃብት ወደ ተደራጀ አቅም ለመለወጥ እየሰራ ይገኛል፡፡

በግብርና፤ በአምራች ኢንዱስትሪ፤ በቱሪዝም፤ በማዕድን፤ በአገልግሎትና ሎጀስቲክስ ዘርፍ ከቅርብ አመታት ወዲህ የተሰሩት ስራዎች እና የተገኙት ዉጤቶች ኢትዮጵያ ያሏትን ጸጋዎች በአግባቡ መጠቀም ከቻለች በአጭር ጊዜ ዉስጥ ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት እንደምትችል የሚያላክት ነዉ፡፡

በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እና በሌሎች የግብርና ልማት ስራዎች፤ ዕሴት የተጨመረባቸዉ እና አዳዲስ ምርቶችን በማምረት፤ የጀማሪ ድርጅቶችን የፈጠራ ሃሳብ በማበረታታትና ለገበያ እንዲቀርቡ በማድረግ አበረታች ዉጤት ማምጣት ተችሏል፡፡

በዓለም ኢኮኖሚ ዉስጥ ተወዳዳሪ የሆኑ ምርቶችን በብዛትና በጥራት ከማምረት ረገድ እየታየ ያለዉ ዉጤትም የግሉ ዘርፍ አቅሙን አሟጦ መጠቀም ከቻለ አስተማማኝ ኢኮኖሚ መገንባት እንደሚቻል የሚያረጋግጥ ነዉ፡፡

የመደመር መንግሥት ችግሮችን ወደ ዕድል እንዲሁም የመበልጸግ ዐቅሞችን ወደ ዉጤት ለመቀየር በያዘዉ ራዕይ ሃገሪቱ በሁሉም ዘርፎች ያላትን እምቅ ሃብቶች ወደ ምርትና ምርታማነት በመቀየር አመርቂ ዉጤት በማስመዝገብ ላይ ትገኛለች፡፡

ከቅርብ አመታት ወዲህ የግብርና ምርቶችንና ማዕድናትን ጨምሮ የተለያዩ ሃገራዊ ምርቶችን በማቀነባበር እና እሴት በመጨመር ወደ ዉጪ ሃገራት በመላክ የዉጭ ምንዛሬን በእጅጉ ማሳደግ ተችሏል፡፡

ሃገሪቱ ያላትን ጸጋዎችና አንጡራ ሃብቶች በማሰባሰብ፤ ወደ ተደራጀ ሃገራዊ አቅም በመቀየርና ቀጣይነት ያለዉ ዉጤት በማስመዝገብ ሂደት ዉስጥ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ እድል ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ የቴክኖሎጂ ሽግግርንም መፍጠር ተችሏል፡፡

ግብርናን ጨምሮ በተለያዩ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚመረቱ ምርቶች ለሸማቹ ኀብረተሰብ አማራጭ ገበያን የፈጠሩ ሲሆን ዋጋን ከማረጋጋት ረገድም የላቀ ሚና አላቸዉ፡፡

የመደመር መንግሥት ሃገሪቱ ያላትን ዕምቅ አቅሞች በማሰባሰብ እና ወደ ዉጤት በመቀየር ዘላቂ ሃብትን ለመፍጠር እየተከተለ ያለዉ መንገድ ዘርፈ ብዙ ዉጤቶችን ከማስመዝገቡም በላይ ቀጣይነት ያለዉ ኢኮኖሚን ለመገንባት፤ ብልጽግናን ለማረጋገጥና የኢትዮጵያን ስልጣኔ እዉን ለማድረግ ጠንካራ መሰረት የሚጥል እሳቤ ሆኗል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review