ለዜጎች ክብር የተሰጠ ዋጋ

You are currently viewing ለዜጎች ክብር የተሰጠ ዋጋ

“አዲስ አበባ በሰው ተኮር ሥራዎቿ ተምሳሌት ሆናለች”
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ

“ቅስሙ በገበያ እንዳይፈስ፣ ወንድ ልጅ ብቻውን ነው እሚያለቅስ” እንዲል፣ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን የብሌን አባት ወጣት አሸናፊ አሰፋ “ከዐይኑ ብሌን ጣር ተመጦ፤ ከአንጀት ሲቃ ተቆርጦ” እንዲያ ነው! ለልጁ ሲል የመከራን ዳገት የገፋው፤ የኑሮን ሁዳዴ ያጋመሰው፡፡ አዎ! ሎሬቱ ቀድሞ እንዳመሰጠረው አንጀቱን በአንጀት ነው፣ የታጠቀው፡፡

ይህ ብርቱ አባት እንደሚለው ብሌን፣ ከተወለደች አርባ ቀን ጀምሮ ባጋጠማት የጭንቅላት እክል አልጋ ላይ ውላለች፡፡ “ብሌን ለእኔ ልጄ ብትሆንም ለእግዚአብሔር ደግሞ የእጁ ሥራ ናት። እኔ ሞግዚቷ ነኝ፡፡” ይላል መከራው ቢከብድም ልጅን ማሳደግ የአባትነት ወጉ መሆኑን ሲገልፅ፡፡

ለልጁ ሲል የሹፍርና ሥራውን ትቶ ወደ ፅዳት ሥራ የገባው የብሌን አባት፣ ሁሌም ሌሊት ሌሊት ጨለማና ምድር በወጉ ሳይሰነባበቱ ከቤት ይወጣና፣ ሥራውን አከናውኖ ረፋድ ሦስት ሰዓት ግድም ይመለሳል፡፡ ለምን ቢሉ፣ መናገርም መራመድም እንዳትችል ካደረጋት የህመም ስቃይ ጋር በዝምታ የልጅነት ጊዜዋን እየገፋች ያለች የበኩር ልጁን ሊንከባከብ፡፡

ወጣት አሸናፊ ከአሳዛኝ የሕይወት ምዕራፎቹ መካከል ይህንን ሲያስታውስ ልቡ እያነባ መሆኑን የፊቱ ገፅታ ያሳብቅበታል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፣ የብሌን ታናሽ እህት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ትምህርት ቤት ስትገባ ‘ከእህቴ ጋር ካልሆነ ወደ ትምህርት ቤት አልሄድም አለች’ አባት እጅግ ተጨነቀ፡፡ ደግሞም ልጁን በሆነ ነገር ማሳመን እንዳለበት አሰበ፡፡ “አንቺን ትምህርት ቤት ካስገባሁ በኋላ ነው እሷን የማደርሳት” ብሎ አሳመናት፤ እሱ ግን ተደብቆ ከልቡ ፈንቅሎ የወጣውን የእምባ ጎርፍ በጉንጮቹ ላይ አፈሰሰ፡፡

ታዲያ በወቅቱ ይህንን ሁኔታ የሚገልፀው ተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ ሚዲያ  መሰራጨቱን ተከትሎ ‘አባት ግን እናት መሆን ይችላል ለካ’ የሚሉና መሰል  አስተያየቶች በማህበራዊ ሚዲያው ሰሌዳ ላይ ተደጋግመው ተፅፈዋል፡፡

ወጣት አሸናፊ አሰፋ ለአስር ዓመት የአልጋ ቁራኛ የሆነች ልጁን፣ አቅመ ደካማ እናቱን እና እህቶቹን የብሌንንም ታናሽ እህት በተከራያት ጠባብ ቤት ውስጥ ዓመታትን በስቃይ አሳልፏል፡፡

ዛሬ ግን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይህንን ታሪክ ቀይሮታል፡፡ በልደታ ክፍለ ከተማ ሳር ቤት አካባቢ ከተገነቡ ዘመናዊ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ አንዱን ለብሌን አባት አበርክቷል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ብሌን፣ የተሻለ ህክምና የምታገኝበትንም ዕድል አመቻችቷል፡፡

ባሳለፍነው ረቡዕ (መጋቢት 2 ቀን 2018 ዓ.ም) በልደታ ክፍለ ከተማ የተገነባው ዘመናዊ የመኖሪያ ህንፃ፣ ለማህበራዊ ችግር ለተጋለጡ ወገኖች፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ፣ ለአካል ጉዳተኞች እና የሀገር ባለውለታዎች ተላልፏል፡፡ በዚሁ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በልደታ ክፍለ ከተማ የገነባነውን ዘመናዊ የጂ+4 የመኖሪያ ህንፃ፣ ለማህበራዊ ችግር ለተጋለጡ ወገኖች፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ፣ ለአካል ጉዳተኞች እና የሀገር ባለውለታ ለሆኑ ነዋሪዎቻችን በክብር ማስተላለፋቸውን ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም በተለያዩ የልማት ሥራዎች ለተነሱ፤ በቀበሌ ቤት ውስጥ በደባልነት፣ በጥገኝነትና በላስቲክ ቤት ውስጥ ይኖሩ ለነበሩ እንዲሁም የመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ በላያቸው እያለፈ እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ለነበሩ ወገኖቻችን ጭምር ቤት አስረክበናል ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ አዲስ አበባ በሰው ተኮር ሥራዎቿ ተምሳሌት እንደሆነችም ተናግረዋል፡፡

አክለውም ሰው ተኮር ሥራዎችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስጀምረው  መመሪያ ከሰጡበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 7 ዓመታት በሰው ተኮር እሳቤያችን እና በበጎነት አገልግሎት ተሳትፎ ከ45 ሺህ በላይ ቤቶችን ለአቅመ ደካሞች መገንባት ችለናልም ብለዋል።

በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር በ4 ወራት አጭር ጊዜ ውስጥ የተገነባው ይህ የመኖሪያ ቤት፣ 5 ነባር ቤቶችን በማንሳት 70 አባወራዎች ቤት እንዲያገኙ ያደረገ ነው። ይህም ከእጦት መንፈስ ወጥቶ ቦታን በአግባቡ በመጠቀም ትልቅ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል የሚያሳይ መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባዋ፣ ግንባታውም የጥራት ደረጃውን የጠበቀ፣ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ፣ የዜጎችን ክብር የሚመጥንና የቤት ቁሳቁስ የተሟላለት ዘመናዊ ህንፃ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

አክለውም፣ ከተማችን ለሁላችንም ትበቃለች፤ መተሳሰብና ፍቅር ካለ ደግሞ ይበልጥ መስራት ይቻላል። በቀጣይም ለብዙዎች ለመድረስ በትጋት እንሰራለንም ብለዋል፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የቤት ችግር ዓለም አቀፋዊ ነው፡፡ ለአብነትም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እ.ኤ.አ ጥቅምት 20 ቀን 2023 በኒው ዮርክ ከተማ ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤ  “UN expert urges action to end global affordable housing crisis” በሚል ርዕስ  ሰፋ ያለ ጥናት በዘርፉ ባለሙያዎች ቀርቦ ነበር፡፡ በዚህ ጥናታዊ ሪፖርት መሠረትም በዓለማችን ቤት መስራት አሊያም መግዛት የማይችሉ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ነው፡፡

ይህንንም ተከትሎ በዓለማችን በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የመኖሪያ ቤት ወጪያቸውን መክፈል ባለመቻላቸው ብቻ ከቤት ንብረታቸው እንደሚፈናቀሉ፣ ይህም ለቤት እጦት መባባስ አስተዋጽኦ ስለማድረጉም በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

በመሆኑም በዓለም ዙሪያ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ህዝብ በቂ የመኖሪያ ቤት እና መሠረታዊ አገልግሎቶች እንደሌለው የጠቆመው ሪፖርቱ ይህም በ2030 ወደ 3 ቢሊዮን ሊደርስ እንደሚችል በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡

በመሆኑም ይላል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የቀረበው የባለሙያዎች ጥናታዊ ሪፖርት “አስተዳደሮች፣ መንግሥታዊ ድርጅቶች እና ተቋማት የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመፍታት የበለጠ የተቀናጀ ጥረት ማድረግ አለባቸው” ይላል፡፡

በዓለማችን የተለያዩ አካባቢዎች አሳሳቢ የሆነው የቤት ችግር በአዲስ አበባ ከተማም የሚታይ ስለመሆኑ ከላይ ካነሳናቸው ሀቆች ባሻገር ብዙ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህንን በውል የተረዳው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም በጋራ መኖሪያ ቤቶች ከሚያከናውነው ቤቶች ግንባታ በተጨማሪ የተለያዩ ባለሀብቶችን እና በጎ ፈቃደኛ ዜጎችን በማስተባበር አዳዲስ ቤቶችን በመገንባትና ሊወድቁ የደረሱ ደሳሳ ጎጆዎችን በአዲስ መልክ ቀና በማድረግ የበርካቶችን እምባ እያበሰ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት በወራቤ ዩኒቨርሲቲ  የማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር አንዋር ጫሚሶ እንደገለፁት እንዲህ አይነት ሰው ተኮር ተግባራት ማህበራዊ መስተጋብሩን እውን ለማድረግ እንደሚያግዙና  የሀገሪቱን ልማት በተሻለ መሠረት ላይ ለማንበርም ትልቅ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

የማህበራዊ ሳይንስ ምሁሩ እንደሚሉት ብልፅግናን ለማረጋገጥ እንደ ሀገር ከተቀመጡት የዘላቂ ልማት ግቦች መካከል አንዱ አካታች የሆነ እድገት ማምጣት ነው፡፡ ይሄውም ሴቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን ወይም ለተለያዩ ማህበራዊ እና መሰል ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን አካታች በሆነ መልኩ መስራት ሀገራችን አሁን የምታደርገውን ጥረት ሙሉ ለማድረግ ያግዛልም ብለዋል፡፡

ቀደም ሲል ይህን መሰል ተግባራት ላይ ተሰማርተው የምናያቸው መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ነበሩ ያሉት የማህበራዊ ሳይንስ ምሁሩ አሁንም ቢሆን እነዚህ ተቋማት በተለያዩ ሀገሪቱ ክፍሎች ያሉ ቢሆንም እንደ አዲስ አበባ ባሉ ትልልቅ ከተሞች የሚታዩ ማህበራዊ ችግሮችን ይሸፍናሉ ማለት አይቻልም፡፡ ለአብነትም አዲስ አበባ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለስራ ዕድል፣ ለተሻለ ኑሮ ፍለጋ እና በሌሎች በርካታ ጉዳዮች የሚፈልሱባት ከተማ ናት፡፡ በመሆኑም መንግስት ይህንን ጉዳይ ትኩረት በመስጠት መሥራቱ በጣም ትልቅ ነገርና እንደ ሀገርም ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጣ የሚያስችል ተግባር ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰቡን መሠረታዊ ችግሮች ለመቅረፍ እየተሰሩ ያሉ ዘርፈ ብዙ ልማቶች የሚበረታቱ መሆናቸውን የጠቆሙት የማህበራዊ ሳይንስ ምሁሩ አንዋር ጫሚሶ፣ ይህን መሰል ተግባር በቀጣይነት መልኩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥረት ማድረግና ማገዝ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው አቶ ሶፎንያስ ፍሰሃ በበኩላቸው፣ ከተማዋ በተስፋ ብርሃን እና በተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር፣ በቤቶች ዕድሳት እና ለተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሚዘጋጁ የማገገሚያ ማዕከላት የተጋላጭ ወገኖችን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡

ባሳለፍነው ረቡዕ በልደታ ክፍለ ከተማ ከተገነባው ዘመናዊ የጂ+4 የመኖሪያ ህንፃ፣  የቤት ባለቤት ተጠቃሚ ከሆኑ የመዲናዋ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ መስከረም ሰለሞን አንዷ ናቸው፡፡ ትናንት እንደነገሩን በተቀለሰች ከላይም ከታችም በምታፈሰው በዚያች ደሳሳ ጎጆ ውስጥ የስቃን ገፈት የመከራን ዳገት መውጣትና መውረዳቸውን ሲያስታውሱ የሚያቃጥል የሀዘን እንባ በጉንጫቸው በረንዳ ይፈስሳል፡፡ ችግራቸውን በውል ተረድቶ ከተማ አስተዳደሩ የሰጣቸውን የዛሬውን ውብና ምቹ ቤት ሲያስቡ ደግሞ ከሀዘን ስሜታቸው ድንገት ይወጡና ደስታቸው ወደር እንደሌለው የፊታቸው ገፅታ ከቃላት በላይ ይናገራል፡፡

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review