AMN- መጋቢት 8/2018 ዓ.ም
ከገበሬ ቤተሰብ ተወልደው በራሳቸው ጥረትና ተሰጥኦ የኢትዮጵያን ስም በዓለም አቀፍ የኪነ-ጥበብ መድረክ ከፍ ያደረጉት አንጋፋው ሰዓሊ ሻምበል ለማ ጉያ፣ በዘርፉ አዲስ አሻራ ማሳረፋቸውን ቀጥለዋል።
በቢሾፍቱ ከተማ የሚገኘው የሰዓሊው የጥበብ ጋለሪ፣ የሀገሪቱን ባህላዊና ማህበራዊ እሴቶች ለዓለም የሚያስተዋውቅ ቀዳሚ ማዕከል ሆኗል።
የአርቲስቱ ልጅ ሰዓሊ ዳዊት ለማ እንደገለጹት፣ አርቲስት ለማ ጉያ በቢሾፍቱ ከተማ የመሰረቱት የቆዳ ስዕል ማዕከል በርካታ ተተኪዎችን በማፍራት ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
በማዕከሉ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር የመጡ በርካታ ወጣቶች ጥበቡን እየተማሩ እንደሚገኙና የአርቲስቱን ፋና እየተከተሉ እንደሆነም ሰዓሊ ዳዊት ለማ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
የሻምበል ለማ ጉያ ሥራዎች ልዩ መታወቂያቸው በቆዳ ላይ የሚሰሩባቸው ጥበባዊ ዘዴዎችና የቆዳውን ተፈጥሯዊ ቀለም ሳይቀይሩ ምስሎችን የመሳል አዲስ የፈጠራ ስልት ለስነ-ጥበብ ዓለም አበርክተዋል።
በተጨማሪም እንደ ብርቱካንና ሎሚ ያሉ ተፈጥሯዊ ፍራፍሬዎችን ለጥበብ ስራዎች በመጠቀም ልዩ ቀለምና ቅርጽ መፍጠር እንደሚቻል በተግባር አሳይተዋል።
በቢሾፍቱ የሚገኘው የለማ ጉያ የጥበብ ጋለሪ ሥራዎቹን ለተመልካች ከማቅረብ ባለፈ እንደ ትልቅ የትምህርት ማዕከል እያገለገለ ይገኛል።
ሰዓሊው በሕይወት ዘመናቸው በራሳቸው ስቱዲዮ ውስጥ በርካታ ተተኪዎችን በማሰልጠን ለሙያው እንዲበቁ ያደረጉ ሲሆን፣ ማዕከሉም የኪነ-ጥበብ ውጤቶች የሚተዋወቁበትና ታሪክ የሚዘከርበት ስፍራ ሆኗል።
እያንዳንዱ ሥራቸው ባህላዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ መልዕክቶችን በውስጡ የያዘ ሲሆን፣ በተለይም ለወጣት ሰዓሊዎች የመነሳሳትና የልምድ መለዋወጫ መድረክ በመሆን እያገለገለ ነው።
ሻምበል ለማ ጉያ በፅናትና በፈጠራ የታጀበው ህይወታቸው ለብዙዎች አርአያ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የጥበብ ማዕከላቸው ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ጎብኚዎች በሩን ክፍት አድርጎ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
በበረከት ጌታቸው