ቤተ ክርስቲያን ከመንግስት ጋር ተባብራ እንዳትሰራ የሚከለክለዉ ማነዉ?

You are currently viewing ቤተ ክርስቲያን ከመንግስት ጋር ተባብራ እንዳትሰራ የሚከለክለዉ ማነዉ?

AMN — መጋቢት 8/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “የሃይማኖት ተቋማት በመደመር መንግስት እይታ” በሚል መሪ ሀሳብ በመዲናዋ ከሚገኙ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማትና አባቶች ጋር ምክክር እያካሄደ ይገኛል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የእምነት አባቶች ጋር ዉይይት ያካሄዱ ሲሆን ተሳታፊዎችም በከተማ፣ በሃገር አቀፍ ደረጃ እና እንደ ሃይማኖት ተቋም እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን አስመልክቶ የተለያዩ ሃሳብ፣ አስተያየትና ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡

ተሳታፊዎቹ እንደገለጹት አንድ የሃይማኖት ተቋም ከመንግስት ጋር አብሮ መስራቱ ለመንግስትም፣ ለሃይማኖት ተቋምም፣ ለትዉልድ ግንባታም፣ ለሃገራዊ ሰላምና ልማት ትልቅ ጠቀሜታ አለዉ፡፡

እንደ ሃይማኖት ተቋሙ አስተምህሮ ለመንግስት መታዘዝን የሚፈቅድ እንጂ የሚከልክል ህግ ስለሌለ የሃይማኖት ተቋማት ከመንግስት ጋር አብረዉ መስራት ይጠበቅባቸዋል ያሉት ተሳታፊዎቹ አንዳንድ አካላት ግን ቤተ ክርስቲያኗ ከመንግስት ጋር አብራ እንዳትሰራ ያደርጋሉ፤ ቤተ ክርስቲያን ከመንግስት ጋር አብራ እንዳትሰራ የከለከለዉ ማነዉ? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ከለዉጡ ወዲህ በአዲስ አበባ ከተማ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት መገንባታቸዉን እና አግባብነት ያላቸዉ ቤተ ክርስቲያን ጥያቄዎችም ምላሽ በማግኘት ላይ መሆናቸዉን ያነሱት ተሳታፊዎቹ የአመራሩን ቁርጠኝነት አድንቀዋል፡፡

በልማቱም ረገድ በ24/7 የስራ ባህል በወንዝ ዳርቻ እና በኮሪደር ልማት በተሰሩ በርካታ የልማት ስራዎች፣ በቆሻሻ እና ጽዳት ችግር የምትታወቀዉ አዲስ አበባ ንጹህ፣ ጽዱና ለመኖር ምቹ ሆናለች፤ የወንጀለኞች መደበቂያ የነበሩ አካባቢዎች የህጻናት መጫዎቻና የመዝናኛ ስፍራ ሆነዋል፤ ቤተ ክርስቲያንም የልማቱ ተጠቃሚ ሆናለች ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ወደ ሌሎች ክልሎች እየተስፋፉ መሆናቸዉን ያነሱት ተሳታፊዎቹ የተጀመረዉ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በምገባ አገልግሎት፣ አቅመ ደካማ ዜጎችን የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ በማድረግ እና የወደቁትን በማንሳት እያከናወነ ላለዉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች የሃይማኖት አባቶቹ እዉቅና ሰጥተዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ከቤተ ክርስቲያኗ ጋር በትብብር በመስራቱ የሃይማኖት በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ተደርጓል፤ ይህም ለቱሪዝም እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነዉ፤ ከባህረ ጥምቀት ቦታዎች ጋር ተያይዘዉ ሲነሱ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ምላሽ ማግኘት ጀምረዋል፡፡

ተሳታፊዎቹ ከይዞታ ማረጋገጫ እና ከግብር አከፋፈል ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ ቢፈታ ያሏቸዉን የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review