በአዲስ አበባ በስድስት ወራት ውስጥ ከ5 ሺህ 800 በላይ ፍቺዎች ተመዝግበዋል

You are currently viewing በአዲስ አበባ በስድስት ወራት ውስጥ ከ5 ሺህ 800 በላይ ፍቺዎች ተመዝግበዋል

AMN – መጋቢት 9/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በስድስት ወራት ውስጥ 19 ሺሕ 800 ጋብቻዎች እና 5 ሺሕ 805 ፍቺዎች መመዝገባቸውን የከተማዋ የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ አስታውቋል።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጥጋቡ ሹመይ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል በሰጡት ማብራሪያ፤ ለተለያዩ ማኅበራዊ አገልግሎቶች የፍቺ ማስረጃ እንደ ቅድመ ሁኔታ መጠየቁ የዘገዩ ፍቺዎች እንዲመዘገቡ አስችሏል፡፡

በዚህም ከተመዘገቡት ፍቺዎች መካከል 1 ሺሕ 750 ያህሉ ፍቺ በተፈጸመ በ30 ቀናት ውስጥ የተመዘገቡ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ 695ቱ ደግሞ ዘግይተው የተመዘገቡ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ይህም የምዝገባ ቁጥር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከሁለት ሺህ በላይ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።

ከፍቺ በስተጀርባ ስላሉ ምክንያቶች ማብራሪያ የሰጡት የህግና ማህበራዊ ጉዳይ አማካሪ ወ/ሪት መቅደስ አስፋው፤ በትዳር ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮች ድንገተኛ ሳይሆኑ፣ ይስተካከላሉ በሚል ቸልተኝነት ትኩረት ሳይሰጣቸው የታለፉ ጉዳዮች ውጤት መሆናቸውን ገልጸዋል።

አማካሪዋ አክለውም ጋብቻን መመሥረትም ሆነ ማፍረስ የተጋቢዎች ምርጫ ቢሆንም፣ ከፍቺ በኋላ የሚመጡትን አውዳሚ ውጤቶች ግን በቀላሉ መቆጣጠር እንደማይቻል ገልጸዋል።

ፍቺ በቀጥታ ግለሰቦችንና ልጆችን የሚጎዳ ሲሆን፣ በተዘዋዋሪ ደግሞ የሀገር መሠረት የሆነውን ቤተሰብ የሚንድ ተግባር መሆኑን አስረድተዋል።

ጤናማ ዜጋ ሊገኝ የሚችለው ከጤናማ የትዳርና የቤተሰብ መዋቅር ነው ያሉት አማካሪዋ፤ ሕፃናት የወላጆቻቸውን የሕይወት ትግልና መከራ እያዩ እንዲያድጉ መገደዳቸው የማንነት ጥያቄ እንዲፈጠርባቸው ያደርጋል ብለዋል።

ይህም ልጆቹ አሻግሮ ስለ ማኅበረሰብ ከማሰብ ይልቅ ራስን በማዳን ወይም ግለኝነት ውስጥ እንዲወድቁ የሚያደርግና የሀገርን የብልጽግና ጉዞ የሚያቀነጭር መሆኑን ወ/ሪት መቅደስ አስገንዝበዋል።

የፍቺ ቁጥርን ለመቀነስና ሕፃናትን ከሥነ-ልቦና ቀውስ ለመታደግ ትልቁ መፍትሔ የቅድመ ጋብቻ ዝግጅት መሆኑን የጠቀሱት አማካሪዋ፤ ተጋቢዎች ትዳር ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ለኃላፊነት ዝግጁ መሆናቸውን ማረጋገጥ እና ያሉባቸውን የግልም ሆነ የአካባቢ ተጽዕኖዎች አስቀድመው መለየት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review