ባደጉት ሃገራት ያየነዉን እና ስንመኘዉ የነበረዉን ልማት በሃገራችን ለማየት በቅተናል – የሃይማኖት መሪዎች

You are currently viewing ባደጉት ሃገራት ያየነዉን እና ስንመኘዉ የነበረዉን ልማት በሃገራችን ለማየት በቅተናል – የሃይማኖት መሪዎች

AMN መጋቢት 9/2018 ዓ.ም

ባደጉት ሃገራት ያየነዉን እና ስንመኘዉ የነበረዉን ልማት በሃገራችን ለማየት በቅተናል ሲሉ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን፣ የካቶሊክ እና ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያናት መሪዎች ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “የሃይማኖት ተቋማት በመደመር መንግስት እይታ” በሚል መሪ ሀሳብ ከኢትዮጵያ ወንጌላውያን፣ ከካቶሊክ እና ከሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያናት መሪዎች ጋር ዉይይት አካሂዷል፡፡

የሃይማኖት አባቶቹም ከለዉጡ ወዲህ ከእምነት እና ከቀብር ቦታ ጋር የተያያዙ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ እየተቀረፉ መምጣታቸዉን በማንሳት ሌሎች ያልተመለሱ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ጠይቀዋል፡፡

ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘም ከአሁን በፊት ከነበረዉ ከፍተኛ መሻሻል ቢኖርም በአንዳንድ ክፍለ ከተሞች እና ወረዳዎች የሚታየዉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ትኩረት ሊሰጠዉ ይገባል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በልማቱ ዘርፍ ካሰበችበት ባትደርስም ከነበረችበት ቦታ በብዙ ምዕራፍ ከፍ ብላለች ያሉት የሃይማኖት መሪዎቹ በተለይ በአዲስ አበባ የታየዉ እድገትና ልማት የጎረቤትና የአለም ሃገሮች መጥተዉ እንዲያዩ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በ24/7 የስራ ባህል የተለያዩ የልማት ስራዎችን በአጭር ጊዜ ዉስጥ በማከናወን ሌብነትን እየተበቀለ ነዉ ያሉት የሃይማኖት መሪዎቹ ፤ የለዉጡ አመራር በሙስናና ብልሹ አሰራሮች ላይ ቆራጥ እርምጃ ባይወስድ ኖሮ ልማቱ ሊመጣ አይችልም፡፡

አዲስ አበባ አሁን ላይ በልማቷም ሆነ በአስተማማኝ ደህንነቷ እንደ ስሟ ዉብ አበባ ከመሆን አልፋ የምታጓጓ ከተማ መሆኗንም የሃይማኖት መሪዎቹ መስክረዋል፡፡

አሜሪካና አዉሮፓን ጨምሮ በሌሎች የዉጭ ሃገራት ስንመኝ የነበረዉን ልማት ዛሬ በሃገራችን ለማየት በቅተናል ያሉት የኢትዮጵያ ወንጌላውያን፣ የካቶሊክ እና የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያናት መሪዎች ኢትዮጵያ በተለያዩ ፈተናዎች ምክንያት አንቀላፍታ ከነበረችበት ነቅታ ተነስታለች ብለዋል፡፡

የለዉጡ መንግስት በሃገሪቱ ለሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት ለሰጠዉ ትኩረት እና በልማቱ ዘርፍ ላስመዘገበዉ ዉጤት የሃይማኖት መሪዎቹ እዉቅና ሰጥተዋል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review