AMN – መጋቢት 10 /2018 ዓ.ም
በመካከለኛዉ ምስራቅ ከተፈጠረዉ የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ባልተለመደ መልኩ እየናረ ይገኛል፡፡
በርካታ የዓለም ሃገራትም የጸጥታ ችግሩ መፍትሔ እስከሚያገኝ ድረስ የነዳጅ ዋጋ መጨመር ጫናን እና ተጽዕኖን ለመቋቋም የተለያዩ እርምጃዎችን እና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በመተግበር ላይ ይገኛሉ፡፡;
ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች ሃገራት ቀደም ብለዉ የጀመሩት በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ ኤሌክትሪክ የማሸጋገር እና በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን መጠቀም ተጠቃሽ ነዉ፡፡
ከአራት ዓመታት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመረው የአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክት፣ እንዲሁም ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እየተደረገ ያለው ሂደት አሁን ላይ ለተከሰተው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ጫና ብቸኛውና ዘላቂ መፍትሔ ሆኗል፡፡
ነዳጅን በቁጠባ የመጠቀም ባህልን ማዳበር በርካታ ሃገራት ልዩ ትኩረት ሰጥተዉ እየተገበሩት ከሚገኙ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ሌላኛዉ ሲሆን ይህም የነዳጅ ዋጋ መናርን ለመቋቋም ትልቅ መፍትሔ እየሆነ ይገኛል፡፡

የጉዞ እቅድ ማዉጣት፤ ጉዞዎችን ማቀናጀት፤ አማራጭ መንገዶችን መጠቀም፤ የትራፊክ ፍሰት የሚቀንስባቸውን ሰዓታትን መርጦ መጠቀም እና መንቀሳቀስ ነዳጅን በቁጠባ ለመጠቀም በመፍትሔነት ይጠቀሳሉ፡፡
አማራጭ የትራንስፓርት ዘዴዎችን ከመጠቀም ጋር በተያያዘም ወደ ተመሳሳይ አቅጣጫ ከሚጓዙ ጓደኞች ወይም የሥራ ባልደረቦች ጋር በመቀናጀት የአንድ መኪና አጠቃቀምን ማበረታታት፤ ለረጅም ርቀት ከግል ተሸከርካሪዎች ይለቅ የሕዝብ ትራንስፖርትን መጠቀም፤ ለቅርብ ርቀት መኪና ከመጠቀም ይልቅ በእግር ወይም በብስክሌት መጓዝ እንደ መፍትሔነት የሚጠቀሱ ናቸዉ፡፡
ይህም ለጤና ጠቃሚ ሲሆን ተጨማሪ ወጪዎችን ከማዉጣት ይታደጋል፡፡ በተለይም አዲስ አበባን የመሰሉ ከተሞች ለእግር እና ለብስክሌት ጉዞዎች ምቹ በመሆናቸዉ አማራጭ የትራንስፖርት ዘዴዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ያግዛሉ፡፡
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ነዳጅን በቁጠባና በብልህነት መጠቀም ለገንዘብ ቁጠባ ብቻ ሳይሆን፣ የተሽከርካሪዎችን እድሜ ለማራዘም እና የአየር ብክለትን ለመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸዉ፡፡
አሁን በአለም ላይ ከተከሰተዉ የጸጥታ ችግር እና የነዳጅ ዋጋ መናር ጋር በተያያዘ ነዳጅን በቁጠባ የመጠቀም ባህልን ማዳበር አማራጭ መፍትሔ ነዉ፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ