AMN መጋቢት 10/ 2018 ዓ.ም (ኢ.ፌ.ፖ.ሚ)፦
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ በተደረገ ጠንካራ ኦፕሬሽን የሀገርና የህዝብ ሀብት በሙስና የመዘበሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ከፍተኛ ሀብት ማዳንና ማስመለስ መቻሉን ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ እና በፀረ ሙስና ኮሚሽን መካከል በተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ መሠረት የሙስና ወንጀሎችን በመከላከልና በመመርመር ሙሰኞችን ለፍትህ በማቅረብ ረገድ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን ከፌደራል የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጋር ተገምግሟል፡፡
ኮሚሽነር ጀነራል ከፍተኛ ክፍተት ይታይበት የነበረውን የሙስና ወንጀሎችን የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባርን ለማስተካከል በሪፎርሙ ትኩረት ተሰጥቶ በመሠራቱ ባለፉት የለውጥ አመታት ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን አስታውሰዋል፡፡
ከፌደራል የፀረ-ሙስና ኮሚሽንና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በተወሰደ እርምጃም በሙስና ወንጀሎች የተሳተፉ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ከ53 ቢሊየን ብር በላይ ማስመለስ መቻሉንና ይህም ከሪፎርሙ በፊት በነበሩ አመታቶች ከተመዘገበው ሁለት ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።

ሁለቱ ተቋማት ባለፈው ዓመት በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የጋራ የስምምነት ሰነድ ተፈራርመው ወደ ሥራ በመግባታቸው እንደሀገር በፀረ- ሙስና ትግል ላይ እየታየ ያለው ለውጥ እንደምሳሌ የሚጠቀስና ለሌሎች ሀገራትም ሞዴል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ጥቂት የዓለም ሀገራት የታጠቋቸውን ዘመናዊ የምርመራ መሣሪያዎችን በመጠቀም የምርመራ ሥራችን ግልፀኝነት የሰፈነበትና ዓለም አቀፍ ስታንዳርዱን የጠበቀ እንዲሆን እየተሰራ ነው ብለዋል።
የፌደራል የሥነ-ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር) በበኩላቸው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከልና የምርመራ ሥራን ዘመናዊና ተወዳዳሪ ለማድረግ እያከናወነ ያለው ተግባር እንደ ሀገር የሚያኮራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
እየተፈጠረ ያለው ከፍተኛ አቅም የሙስና ወንጀሎችን በመከላከልና ተግዳሮት የነበሩ የዘልማድ አሠራሮችን በዲጂታል በመተካት ለፀረ-ሙስና ትግል ውጤታማነት የማይተካ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልፀዋል።
ሁለቱ ተቋማት እንደ ሀገር እየተካሄደ ባላው የፀረ- ሙስና ትግል ላይ ቁልፍ ሚና እንዳላቸው አንስተው በጥምረት ባከናወኑት ሥራ ስኬት በማስመዝገብ ሀገራችን ሙስናን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በምትወስደው ጠንካራ ዕርምጃ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትመሰገንና በመልካም ስም የምትነሳ ሆናለች ማለታቸዉን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለኤኤምኤን የላከዉ መረጃ ያመላክታል፡፡