ቦርንማውዝ ከ ማንችስተር ዩናይትድ

You are currently viewing ቦርንማውዝ ከ ማንችስተር ዩናይትድ

AMN- መጋቢት 11/2018 ዓ.ም

ማንችስተር ዩናይትድ በቀጣይ የውድድር ዓመት የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊ የሚያደረገውን ደረጃ ይዞ ለማጠናቀቅ ጥሩ ጉዞ ላይ ይገኛል። ቀያይ ሰይጣናቱ ባሳለፍነው እሁድ የቅርብ ተቀናቃኛቸው አስቶንቪላን ማሸነፋቸው የበለጠ ተስፋ ሰጥቷቸዋል።

ዩናይትድ ማይክል ካሪክን ጊዜያዊ አሰልጣኝ አድርጎ ከሾመ በኋላ ውጤቱ ሰምሮለታል። ከዘጠኝ የሊግ ጨዋታዎች ሰባቱን አሸንፎ ፣ በአንዱ አቻ ሲለያይ ፣ በአንዱ ብቻ ተረትቷል።

ማግኘት ከሚገባው 27 ነጥብ 22ቱን አሳክቷል ፤ ይህም ካሪክ ከመጣ በኋላ የሊጉ ቡድኖች በሰበሰቡት ነጥብ ደረጃ ቢሰራ ዩናይትድ አናት ላይ ይቀመጣል።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚገኘው ዩናይትድ በ31ኛ ሳምንት መርሐግብሩ ወደ ቪታሊቲ ስታዲየም በማቅናት ቦርንማውዝን ምሽት 5 ሰዓት ይገጥማል። ሁለቱ ክለቦች በኦልድትራፎርድ ያከናወኑት የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ በድራማ ታጅቦ 4ለ4 ነበር የተጠናቀቀው። አስደናቂ ብቃት ላይ የሚገኘው ቡርኖ ፈርናንዴዝ በዛሬውም ጨዋታ ልዩነት ፈጣሪ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

የዩናይትዱ አምበል ቦርንማውዝን በገጠመባቸው ስምንት ጨዋታዎች አራት ግብ አስቆጥሮ ፣ አራት ወደ ግብነት የተቀየሩ ኳሶችን ለቡድን አጋሮቹ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።

ማንችስተር ዩናይትድ ወቅታዊ ብቃቱ ጥሩ ቢሆንም ከቦርንማውዝ ጋር ያለው የቅርብ ጊዜ ውጤት ግን የሚያኩራራ አይደለም። በመጨረሻዎቹ አምስት የፕሪሚየር ሊግ ግንኙነት ቦርንማውዝ አንዱንም አልተሸነፈም። ሁለቱን አሸንፎ በሦስቱ አቻ ተለያይቷል።

በዛሬው ጨዋታ በዩናይትድ በኩል ፓትሪክ ዶርጉ ፣ ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ እና ማቴያስ ደሊግት አይሳተፉም።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review