የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ2025/26 የውድድር ዘመን ወደ ማጠናቀቂያው ምዕራፍ ተቃርቧል። ቀሪዎቹ ስምንት ጨዋታዎች በደረጃ ሰንጠረዡ አናት፣ መሃልና ግርጌ የሚገኙ ክለቦችን እጣ ፈንታ የሚወስኑ የሞት ሽረት ፍልሚያዎች የሚስተናገዱባቸው ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የዘንድሮው የፕሪሚየር ሊግ ጉዞ ካለፉት ዓመታት በተለየ መልኩ እጅግ ተለዋዋጭና አስገራሚ ክስተቶች የታዩበት ሆኖ መካሄዱን ቀጥሏል። ገና ከጅምሩ አንስቶ የሊጉ ግዙፍ ክለቦች ነጥቦችን ሲጥሉና በአንጻሩ መጠነኛ ግምት የተሰጣቸው ቡድኖች ደግሞ ድሎችን ሲያስመዘግቡ ታይቷል፡፡ በተለይም የማጥቃት እግር ኳስ የበላይነት በታየባቸው ያለፉት ወራት፣ በርካታ ግቦች የተቆጠሩባቸውና እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ አሸናፊው የማይታወቅባቸው ጨዋታዎች ልዩ የስታዲየም ድባብና ስሜት ሲፈጥሩ ቆይተዋል። ይህ ሂደት ደግሞ ሊጉን በዓለም ላይ ካሉ ውድድሮች ሁሉ ይበልጥ ተመራጭና የማይገመት እንዲሆን አድርጎታል።
ወሳኝ ምዕራፍ ላይ በሚገኘው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አናት ላይ ያለው ሁኔታ ከአስር ያነሱ የጨዋታ ሳምንታት በቀሩበት በዚህ ወቅት የዋንጫ ፉክክሩ፣ ለሻምፒዮንስ ሊግ ቦታ የሚደረገው ትግል እና ከወራጅ ቀጣና ለመውጣት የሚደረገው ፍልሚያ ውጥረት የነገሰበት እና ትኩረትን የሳበ ሆኗል፡፡ በተለይ የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል አንድ ቀሪ ጨዋታ ካለው ማንችስተር ሲቲ በዘጠኝ ነጥብ ርቆ ሊጉን እየመራ ቢሆንም የሊጉ አስገራሚ ተለዋዋጭነት ዋንጫው ወደየት እንደሚያመራ ለመገመት ከባድ ያደርገዋል፡፡
በተለይ አርሰናል እና ማንችስተር ሲቲ በቅርቡ እርስ በእርስ የሚገናኙበት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ የዋንጫውን አሸናፊ የመወሰን ትርጉም ያለው መርሃ ግብር ቢሆንም በወረቀት ላይ በአንጻራዊነት የአርሰናል ቀሪ ጨዋታዎች ቀላል ይመስላሉ፡፡ በተጨማሪም መድፈኞቹ በሊጉ ከሚያደርጓቸው ቀጣይ አምስት ጨዋታዎች አራቱ በኤምሬትስ የሚደረጉ መሆናቸው ይበልጥ ወደ ዋንጫው ለመቅረብ ዕድል የሚሰጣቸው ይሆናል፡፡ በተለይ ደግሞ በዚህ ዓመት በሜዳው በአንድ ጨዋታ ብቻ የተሸነፈው አርሰናል ቀጣይ ከሚያደርጋቸው አምስት ጨዋታዎች አራቱን በሜዳው ማድረጉ ብቻ ሳይሆን የሚያገኛቸው ቡድኖች መካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወይም የመውረድ ስጋት የሌለባቸው መሆኑ ሌላ ዕድል የሚሰጠው ሆኗል፡፡

በተቃራኒው የማንችስተር ሲቲ ቀጣይ አምስት ጨዋታዎች ከባድ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ማንችስተር ሲቲ ቀጣይ ከሚያርጋቸው አምስት ጨዋታዎች መካከል ወደ ምዕራብ ለንደን አምርቶ ከቼልሲ የሚደረገውን ጨምሮ አራቱ ከሜዳው ውጪ የሚያደርጋቸው ናቸው። በተጨማሪም በሜዳው የሚያደርገው አንዱ ጨዋታም ከቀጥተኛ የዋንጫ ተፎካካሪው አርሰናል ጋር ነው፡፡
ሌላኛው በሻምፒዮንስ ሊግ ለመሳተፍ የሚደረገው ጉዞ ነው፡፡ በዚህ ዓመትም አምስተኛ ደረጃን ይዞ የሚያጠናቅቀው ቡድን በሻምፒዮንስ ሊግ የመሳተፍ ዕድል ያለው በመሆኑ፣ ማንችስተር ዩናይትድ፣ አስቶን ቪላ፣ ቼልሲ እና ሊቨርፑል ይሄንን ደረጃ ለማግኝት ትልቅ ፉክክር የሚያደርጉበት ይሆናል። በተለይ በእያንዳንዳቸው መካከል ያለው የነጥብ ልዩነት የተቀራረበ መሆኑ እና እርስ በእርስ የሚገናኙ መሆናቸው ቀሪ መርሃ ግብሮች ከዋንጫው ፉክክር እኩል እንዲጠበቁ ያደርገቸዋል፡፡ 4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው አስቶን ቪላ በቀጣይ የሚያርጋቸው ስድስት ተከታታይ ጨዋታዎች ከ7ኛ ደረጃ በታች ያሉ በመሆናቸው በአንጻራዊነት ቀላል የሚባሉ ናቸው፡፡
ከማይክል ካሪክ በኋላ በብዙ የተቀየረው ማንችስተር ዩናይትድ ቀጣይ ከሚያርጋቸው 6 ጨዋታዎች ሦስቱን ለሻምፒዮንስ ሊግ ቦታ የሚፋለምባቸው መሆናቸው ፈተናውን ከባድ ያደርግበታል፡፡ ከቼልሲ እና ሊቨርፑል ቀሪ ተጋጣሚዎቹ ሲሆኑ ሌላኛው ከባድ ፈተና የሚጠብቀው ቼልሲ ከቀጣይ ስድስት ጨዋታዎች ማንችስተር ዩናይትድ እና ማንችስተር ሲቲን በተከታታይ የሚያገኝበት ይጠቀሳል፡፡ በአንጻራዊነት ሊቨርፑል እድሉን መጠቀም ከቻለ ቢያንስ በወረቀት ላይ ከባድ የሚባሉ አይደሉም፡፡
ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ወልቭስ እና በርንሌይ የተለየ ተዓምር ካልተፈጠረ በስተቀር በሊጉ የመቆየታቸው ነገር ያበቃለት ይመስላል። ነገር ግን ሊድስ ዩናይትድ፣ ቶተንሃም፣ ኖቲንግሃም ፎረስት እና ዌስትሃም ካላቸው የነጥብ መቀራረብ የተነሳ በሊጉ ለመቆየት የሚፋለሙበት ነው፡፡ 15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሊድስ ዩናይትድ ከሌሎቹ አንጻር ቀለል ያሉ ተጋጣሚዎች አሉት፡፡ በተቃራኒው ወራጅ ቀጣናው ውስጥ የሚገኘው ዌስትሀም ምንም እንኳን በቅርቡ እየተሻሻለ ቢመጣም ከማንችስተር ሲቲ፣ ከአስቶን ቪላ እና ከአርሰናል ያልጨረሳቸው የቤት ስራዎች መኖራቸው በሊጉ የመቆየቱን ጉዳይ እጅግ ፈታኝ ያደርግበታል፡፡
ድንገት ራሱን የመውረድ ስጋት ውስጥ ያገኘው ቶተንሃም ሆትስፐርም ከዌስትሃም በአንድ ነጥብ ከፍ ብሎ የተቀመጠ ሲሆን፣ ባለፉት 11 ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች አለማሸነፉ የመትረፉን ነገር ጥያቄ ውስጥ ከቶታል፡፡ የሰሜን ለንደኑ ክለብ ከአስቶን ቪላ እና ከቼልሲ እንዲሁም ቀጥተኛ ተፎካካሪዎቹ ከሆኑት ላለመውረድ ከሚታገሉት ቡድኖች ጨዋታ ያለው መሆኑ ለመቆየት ከባድ የቤት ስራም ይጠብቀዋል፡፡

ላለመውረድ የሚደረገው ትግል በሊጉ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ጥብቅ ፍልሚያ እንደሚሆን ይገመታል። በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ የሚገኙት አምስት ክለቦች በነጥብ ያላቸው መቀራረብ፣ እያንዳንዱን ጨዋታ እንደ ዋንጫ ፍጻሜ እንዲመለከቱት ያደርጋቸዋል። በመጨረሻም፣ የግል ክብረወሰኖች ሰባሪው ኤርሊንግ ሃላንድ በ38 ጨዋታዎች ውስጥ ያስመዘገበውን የጎል ብዛት ራሱ የመስበር ዕድሉ ሰፊ እንደሆነ ኦፕታ (Opta) ያመላክታል።
በአጠቃላይ፣ እነዚህ ስምንት ሳምንታት በታክቲክ ብስለት፣ በአካላዊ ብቃትና በስነ-ልቦና ጥንካሬ ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው፣ የ2025/26 የውድድር ዘመን ማሳረጊያ በታሪክ ማህደር ውስጥ በደመቀ ቀለም እንደሚሰፍር ጥርጥር የለውም።
የ2025/26 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዘመን በሜዳ ላይ ድርጊቶች ብቻ ሳይሆን በቴክኖሎጂና በስታቲስቲክሳዊ መረጃዎችም የታሪክ መፃህፍትን እያደሰ ይገኛል። እንደ ኦፕታ መረጃ የዘንድሮው የውድድር ዓመት በሊጉ ታሪክ ከፍተኛው የጨዋታ ፍጥነት እና የተጫዋቾች የሩጫ ርቀት (High-intensity sprints) የተመዘገበበት ሲሆን፣ ይህም ካለፉት ሁለት ዓመታት በአማካይ በ12 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። በተለይም አሰልጣኞች ከመከላከል ይልቅ ለአጥቂ እግር ኳስ በሰጡት ቅድሚያ ምክንያት፣ በጨዋታው መገባደጃ (ከ90ኛው ደቂቃ በኋላ) የሚቆጠሩ ወሳኝ ግቦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ የሊጉን አስገራሚ ተለዋዋጭነትና የቡድኖችን እስከመጨረሻው የመታገል መንፈስ በግልጽ ያሳያል።
በሌላ በኩል፣ የዘንድሮው የውድድር ዓመት በከፊል አውቶማቲክ የጨዋታ ውጭ መቆጣጠሪያ (Semi-automated Offside Technology) ስራ ላይ መዋልና በቪ.ኤ.አር (VAR) ውሳኔዎች ግልፅነት ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች የውድድሩን ፍሰት መልክ ቀይረውታል። እንደ ፕሪሚየር ሊግ ዳታ ሴንተር መረጃ ከሆነ፣ በዘንድሮው የውድድር ዘመን በሜዳቸው ነጥብ የማይጥሉ ክለቦች ቁጥር መጨመሩና እንደ ትራንስፈርማርኬት ባሉ ምንጮች የሚገለጸው የወጣት ተጫዋቾች የገበያ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ማደግ፣ የሊጉን የፉክክር ሚዛን ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሮታል። እነዚህ ክስተቶች ተዳምረው የ2025/26ን የውድድር ዘመን በፍትሐዊነትና በከፍተኛ ፉክክር የታጀበ ከማድረጋቸው ባለፈ፣ በዓለም ዙሪያ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ተመልካቾችን የሳበ ታላቅ ስፖርታዊ ድራማ አድርገውታል።
የ2025/26 የፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዘመን ማሳረጊያ በሜዳ ላይ ከሚታየው ብርቱ ፉክክር ባለፈ፣ በቴክኖሎጂና በስታቲስቲክሳዊ መረጃዎች የታጀበ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እየፃፈ ይገኛል። ቀሪዎቹ ስምንት ጨዋታዎች ተራ እግር ኳስ ሳይሆኑ፣ የክለቦች የዓመታት ድካም ፍሬ የሚታይባቸውና የደጋፊዎች የልብ ትርታ የሚለካባቸው ወሳኝ ደቂቃዎች ናቸው። ዋንጫው ወደ ሰሜን ለንደን ያመራል ወይንስ በማንችስተር ሰማይ ስር ይቆያል? ለሻምፒዮንስ ሊግ የሚደረገው ሽሚያና ላለመውረድ የሚደረገው የሞት ሽረት ትግልስ በማን ድል አድራጊነት ይጠናቀቃል? መልሱን ለማግኘት የሜዳ ላይ ድራማውን አብረን መከታተላችንን እንቀጥላለን።
በሳህሉ ብርሃኑ