ለየት ያሉና አስገራሚ የኢድ አል-ፈጥር በዓል አከባበሮች በዓለም ዙሪያ

You are currently viewing ለየት ያሉና አስገራሚ የኢድ አል-ፈጥር በዓል አከባበሮች በዓለም ዙሪያ

AMN – መጋቢት 11/2018 ዓ.ም

1447ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በመላው ዓለም በሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ድምቀት እየተከበረ ይገኛል። በዓለም የሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች የረመዳንን ወር በጾም እና በጸሎት ካሳለፉ በኋላ፣ የኢድ አልፈጥርን በዓል በታላቅ መንፈሳዊ ደስታ ይቀበሉታል።

ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ሀገር የራሱ የሆነ የሚገርም እና ለየት ያለ ባህላዊ አከባበር አለው። የረመዳን ፍጻሜ ሆና የኢድ ጨረቃ ስትታይ በዓለም ዙሪያ ያሉ የእምነቱ ተከታዮች በደስታ ትሞላሉ።

በበዓሉ ዕለት በአንዳንድ ሀገራት የሚከናወኑ ድርጊቶች ደግሞ በእጅጉ አስገራሚ ናቸው። ከእነዚህም መካከል፤ የአፍጋኒስታን “የእንቁላል ውጊያ” አንዱ ነው፡፡ የአፍጋኒስታን ወንዶች በዓሉን የሚያከብሩበት አንድ ለየት ያለ መንገድ አላቸው። የተቀቀሉ እንቁላሎችን ይዘው አደባባይ በመውጣት አንዱ የሌላውን እንቁላል ለመስበር በመፋለም ነው።

“ቶክም-ጃንጊ” (Tokhm-jangi) ወይንም “የእንቁላል ውጊያ” ተብሎ በሚጠራው በዚህ ጨዋታ እንቁላሉ ሳይሰበርበት የቀረ ሰው አሸናፊ ይሆናል።

በቻይና – ዝክር እና ቤተሰባዊ ትስስር በቻይና የሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች በዓሉን የሚያከብሩት ወደ ቀድሞ አባቶቻቸውና ሌሎች ቤተሰቦቻቸው መቃብር በመሄድ ነው።

መቃብሮችን በማጽዳት እና ቁርአን በመቅራት ያለፉ ዘመዶቻቸውን ያስባሉ። ይህም በዓሉን ከቤተሰብ ትስስር እና ከትውልድ ታሪክ ጋር በጥብቅ ያገናኘዋል።

የተርኪዬ “የስኳር በዓል”

በተርኪዬ ኢድ አል-ፈጥር “ሸከር ባይራሚ” (Seker Bayrami) ወይንም “የከረሜላ/የስኳር በዓል” ተብሎ ይጠራል።

ልጆች ከቤት ቤት እየዞሩ የጎረቤቶቻቸውን እና የሽማግሌዎችን እጅ በመሳም ሰላምታ ያቀርባሉ፤ አዋቂዎች ደግሞ ለልጆቹ ከረሜላ፣ ቸኮሌት ወይም ባህላዊ ጣፋጮችን በመስጠት በዓሉን በደስታ ያደምቁታል።

የኢንዶኔዥያ “ሙዲክ” (ታላቁ ጉዞ)

ኢንዶኔዥያ፣ “ሙዲክ” የተባለው ባህል ትልቅ ቦታ አለው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከትላልቅ ከተሞች ተነስተው ወደ ተወለዱበት ገጠር ይጓዛሉ።

ይህ ጉዞ በዓለም ላይ ካሉ ትላልቅ ዓመታዊ የሰዎች እንቅስቃሴ ከሚበዛባቸው አንዱ ተደርጎ ይወሰዳል።

የሞሮኮ ባህላዊ ድባብ

በሞሮኮ ወንዶች “ጅላባ” የተባለውን ባህላዊ ልብሳቸውን ለብሰው ወደ መስጂድ ያመራሉ። ከሶላት በኋላ ደግሞ የሞሮኮ መለያ በሆነው የናና ሻይ እና “ምሰመን” በተባለ ባህላዊ ምግብ ከቤተሰብ ጋር ተሰባስቦ የመመገብ ስነ-ስርዓት በዓሉን ለየት ያደርገዋል።

ኢትዮጵያ – አብሮነት እና ማካፈል

በኢትዮጵያ ደግሞ ህዝበ ሙስሊሙ በአንድነት በመሆን የሚያከናውነው የጎዳና ላይ ሶላት፣ የቤተሰብ ጥሪ እና ከተቸገሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የሚደረገው የአብሮነትና ማዕድ የማካፈል ተግባር በዓሉን ልዩ ትርጉም ያላብሰዋል።

እናንተስ ባላችሁበት አካባቢ የኢድ በዓል አከባበርን ለየት የሚያደርገው ምን አይነት ክዋኔ አለ? ሀሳቦትን አጋሩን፡፡

በያለው ጌታነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review