የተፈጥሮ ውበትንና የቤተሰብ መዝናኛን አጣምሮ የያዘው የቡልቡላ ፓርክ

You are currently viewing የተፈጥሮ ውበትንና የቤተሰብ መዝናኛን አጣምሮ የያዘው የቡልቡላ ፓርክ

AMN- መጋቢት 13/2018 ዓ.ም

በከተማዋ እምብርት ሆኖ የገጠሩን አየር የሚያስታውስ፣ ለህፃናት ሳቅና ለታዳጊዎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ምቹ የሆነው አዲሱ የቡልቡላ መዝናኛ ስፍራ ምን አግልግሎቶችን ይዟል ሲል ኤ ኤም ኤን ቅኝት አድርጓል፡፡

ሰዎች የእረፍት ጊዜያቸውን በተለያዩ ተግባራት ያሳልፋሉ። ከእነዚህም መካከል ደግሞ ወጣ ብሎ ከቤተሰብ፣ ከጓደኛና ከዘመድ ጋር በመዝናኛ ስፍራዎች ጊዜን ማሳለፍ ዋነኛው ነው።

በአዲስ አበባ የፓርኮች ቁጥር እየጨመረ በመጣበት በዚህ ወቅት፣ የቡልቡላ ፓርክ ለየት ባለ ድባቡ የብዙዎችን ቀልብ እየሳበ ይገኛል።

ወደ ፓርኩ እንደተገባ በመጀመሪያ የሚቀበለው ሰፊው የህፃናት መጫወቻ ስፍራ ነው። እዚህ ስፍራ ለህፃናት በርካታ አማራጮች ተዘጋጅተዋል።

በትራምፖሊን መዝለል፣ ትናንሽ መኪናዎችን መንዳት፣ በተለያዩ የጫዎታ አይነቶች መዝናናት፣ ህፃናት ከጨዋታው ባለፈ ስዕል በመሳል የፈጠራ ችሎታቸውን እንዲያሳድጉ ዕድል ይሰጣቸዋል።

ልጆች ከእኩዮቻቸው ጋር የሚገናኙበት፣ የሚግባቡበትና ተሯሩጠው የሚጫወቱበት ሰፊ ሜዳ መኖሩ ለስነ-ልቦና እድገታቸው ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።

ቡልቡላ ፓርክ ለታዳጊዎችና ለወጣቶችም የራሱ የሆነ ልዩ ስፍራ አለው። ጤናን ለመጠበቅና የእረፍት ጊዜን በንቃት ለማሳለፍ የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶች ተሟልተውለታል።

የእግር ኳስ፣ የመረብ ኳስ (ቮሊቦል) እና የቅርጫት ኳስ መጫወቻ ስፍራዎች፣ለዋና አፍቃሪዎችም ምቹ የሆነ የዋና ገንዳ ተዘጋጅቷል፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎችም ረጅም ጊዜ የምንንቀሳቀስበት ጤናችንን የምንጠብቅበት እድል አልነበረም በማለት ፓርኩ ለጤናማ የአኗኗር ዘይቤ የፈጠረላቸውን ዕድል ያደንቃሉ።

የፓርኩ ሌላኛው ልዩ መለያው ዘመናዊነትንና ባህላዊነትን አጣምሮ የያዘ ተፈጥሮአዊ ድባቡ ነው። ሲታይ ከተማ ውስጥ ሆኖ ገጠሩንም ይመስላል፡፡ እዚህ ሲመጣ ጭንቀት ያለበት ሰው እንኳን ይረሳዋል ይላሉ ጉብኚዎች፡፡

ፓርኩ በአረንጓዴ ተክሎች የተሸፈነ በመሆኑ፣ በተለይ ከኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ተለይተው ልጆች ስለ ሀገራዊ ተፈጥሮና ባህል እንዲያውቁ ሰፊ ዕድል ይፈጥራል።

ፓርኩ በአካባቢው ለሚኖሩ ነዋሪዎች ረጅም ርቀት ሳይጓዙ እዚያው ሰፈራቸው የሚያገኙት መዝናኛ ነው። ብዙ ወጪ ሳይጠይቅ መላው ቤተሰብ በጋራ ተሰባስቦ እንዲዝናና ያስችላል፡፡ ከከተማው ጫጫታ ወጣ ብሎ ሰፊና አረንጓዴ በሆነ ስፍራ ነፃነትን ለመቀዳጀት ተመራጭ ነው።

የቡልቡላ ፓርክ የደስታ፣ የጤና እና የተፈጥሮ ውበት መገናኛ ሆኖ ጎብኚዎቹን እያስተናገደ ይገኛል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review