አፍሪካዊያን ዓለም አቀፍ የነዳጅ ቀውስ ተፅዕኖን ለመቋቋም የተለያዩ የመፍትሄ አማራጮችን ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል – አሊኮ ዳንጎቴ

You are currently viewing አፍሪካዊያን ዓለም አቀፍ የነዳጅ ቀውስ ተፅዕኖን ለመቋቋም የተለያዩ የመፍትሄ አማራጮችን ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል – አሊኮ ዳንጎቴ

AMN መጋቢት 17/2018 ዓ.ም

የአፍሪካ ቁጥር አንድ ባለጸጋ አሊኮ ዳንጎቴ፣ በመካከለኛው ምስራቅ ባለው ውጥረት ምክንያት የተከሰተውን ዓለም አቀፍ የነዳጅ ቀውስ ተፅዕኖ ለመቀነስ መንግስታት፣ ግለሰቦች እና ኩባንያዎች የተለያዩ የመፍትሔ አማራጮችን በመዉሰድ ላይ እንደሚገኙ ይገልጻሉ፡፡ አንዳንዶቹ እንደ ቁልፍ መፍትሄ እያቀረቡት ያለው ሰዎች ወደ ቤት ውስጥ ሥራ እንዲመለሱ ነው።

እንደ አሊኮ ዳንጎቴ ያሉ ግለሰቦችም አፍሪካዊያን በመካከለኛው ምስራቅ ባለው ውጥረት ሳቢያ የተከሰተውን የነዳጅ ቀውስ ለመቋቋም እንዲህ ዓይነቱን አሰራር ሊከተሉ ይገባል ብለው ያምናሉ።

ዳንጎቴ ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት፣ በቤት ውስጥ መስራት የችግሩን ተፅዕኖ ሊቀንስ ቢችልም፣ ሁኔታው ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው እና መደበኛ ባልሆነው የሥራ ዘርፍ ለሚሰማሩ የቀን ሠራተኞች ግን አስቸጋሪ ሊሆንባቸው እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

በአንዳንድ የአፍሪካ ሃገራት ከባለፈዉ ሳምንት ጀምሮ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ይህም በሌሎች ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ ሊያስከትል ይችላል ተብሎ እንደሚታመንም ተገልጿል፡፡

አፍሪካን ጨምሮ በርካታ የዓለም ሃገራት በነዳጅ አጠቃቀም እና ቁጠባ ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን በመዉሰድ ላይ የሚገኙ ሲሆን በስራ ሰአት እና ቀናት፣ በአማራጭ የትራንስፓርት አጠቃቀም፣ በነዳጅ ቁጥጥር እና መሰል ጉዳዮች ላይ ማሻሻያዎችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ በቤት ውስጥ መሥራት የግለሰቦችን የነዳጅ ፍጆታ በ20% ሊቀንስ እንደሚችል እንዲሁም አገራዊ የነዳጅ አጠቃቀምን እንደሚቀንስ ገልጾ፣ ከግል ተሽከርካሪ ይልቅ የሕዝብ ትራንስፖርትን መጠቀም እንዲበረታታ አሳስቧል።

ተንታኞችን ጠቅሶ ቲአርቲ እንደዘገበዉ፣ እንደነዚህ ያሉ ቀውሶችን በዘላቂነት ለመቋቋም አፍሪካ የራሷን የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካዎች ማስፋፋት እና ሰፊ የኢኮኖሚ ልማት ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርባታል።

ኢትዮጵያ በነዳጅ ግብይት እና ስርጭት ላይ ቀደም ብላ በወሰደቻቸዉ ማሻሻያዎች ተጽእኖዉን ለመቀነስ እየሰራች ትገኛለች፡፡ ከነዳጅ ጥገኝነት ለመላቀቅ እና ብክለትን ለመቀነስ በታዳሽ ኃይል ልማት ዘርፍ የኤሌክትሪክ ኃይልን ከውኃ፣ ከንፋስ እና ከፀሐይ ከማመንጨቷም በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ሃገር ዉስጥ እንዲገቡ የሚያበረታቱ እርምጃዎችን ወስዳለች፡፡

ከወቅታዊዉ የመካከለኛዉ ምስራቅ ግጭት እና የነዳጅ አቅርቦት መስተጓጎል ጋር በተያያዘም አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ነዳጅን በቁጠባ መጠቀም የሚያስችሉ የመፍትሄ አማራጮች እየተተገበሩ ይገኛሉ፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review