የዲሞክራሲ ዋልታ፦ የፖለቲካ ምርጫ ፋይዳ እና ሂደቱ

You are currently viewing የዲሞክራሲ ዋልታ፦ የፖለቲካ ምርጫ ፋይዳ እና ሂደቱ

AMN- መጋቢት 17/2018 ዓ.ም

የዓለም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ፣ የአንድ ሀገር ዕድገትና ሰላም የሚረጋገጠው ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ ሲሆኑ ነው። ከእነዚህ የተሳትፎ መንገዶች መካከል ደግሞ “ምርጫ” ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል።

ምርጫ በባህሪው የዲሞክራሲ ዋልታ ከመሆኑም በላይ፣ ዜጎች የወደፊት ዕጣ ፈንታቸውን በገዛ እጃቸው የሚወስኑበት ትልቅ መድረክ ነው። የፖለቲካ ምርጫ ለአንድ ሀገር ያለውን ዘርፈ-ብዙ ጥቅም እና አንድ ምርጫ ማለፍ ያለባቸውን ወሳኝ ሂደቶች አሉ።

የፖለቲካ ምርጫ ለአንድ ሀገር ዕድገት፣ ሰላምና ሉዓላዊነት ያለው ፋይዳ እጅግ ከፍተኛ ነው። ምርጫ የዜጎች የሥልጣን ባለቤትነት የሚረጋገጥበት ዋነኛው ዲሞክራሲያዊ መንገድ ነው።

ምርጫ ህዝቡ በራሱ ላይ የሚሾማቸውን መሪዎች በነፃነት የሚመርጥበት መድረክ ሲሆን፣ ይህም መንግሥት ከህዝብ የተሰጠ “ህጋዊ ውክልና” (Legitimacy) እንዲኖረው ያደርጋል።

በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ያለ ምርጫ የሚመጣ ሥልጣን በዓለም አቀፍ ሕግም ሆነ በሀገር ውስጥ ተቀባይነት አይኖረውም። ለምሳሌ እንደ ስዊዘርላንድ ወይም ኖርዌይ ያሉ ሀገራት ለረጅም ዘመናት ያካሄዱት ተከታታይ ምርጫ ለሀገራዊ መረጋጋታቸው መሠረት ሆኗል።

በታሪክ የታዩ ብዙ ደም አፋሳሽ ጦርነቶች የሚነሱት በሥልጣን ሽግግር ምክንያት ቢሆንም፣ ምርጫ ግን ይህንን ሽግግር በድምፅ እንጂ በጠመንጃ እንዳይሆን ያደርጋል።

በምዕራብ አፍሪካ እንደ ጋና እና ሴኔጋል ያሉ ሀገራት በተደጋጋሚ በሰላማዊ ምርጫ ሥልጣን በማሸጋገራቸው በቀጠናው ካለው ግጭት ተርፈው ተኩረታቸውን ወደ ኢኮኖሚ እንዲያዞሩ አስችሏቸዋል።

በተጨማሪም ምርጫ መሪዎች ለህዝብ የገቡትን ቃል እንዲያከብሩ ያስገድዳቸዋል። ካልሠሩ በየአራት ወይም በየአምስት ዓመቱ በድምፅ የመሻር ዕድል ስላለ፣ ባለሥልጣናት ለሥራቸው ጥንቃቄ ያደርጋሉ እንዲሁም ተጠያቂነት እንዲኖር ያስችላል ።

ምርጫ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሀገርን ችግር ለመፍታት የያዙትን የተለያየ አማራጭ ለህዝብ የሚያቀርቡበት ሲሆን፣ ህዝቡም የትምህርት፣ የጤና እና የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን በማነፃፀር ለሀገር የሚበጀውን ፓርቲ በመምረጥ የሀገሪቱን ቀጣይ አቅጣጫ እንዲወስን ዕድል ይሰጣል።

የምርጫ ጥቅም የሚረጋገጠው ሂደቱ ነፃና ፍትሐዊ ሲሆን ነው። ሂደቱ የሚጀምረው በመራጮች ምዝገባ ሲሆን፣ ይህም ድምፅ የመስጠት መብታቸው የተጠበቀ ዜጎች በሙሉ እንዲመዘገቡ በማድረግ ሰፊ የህዝብ ተሳትፎ እንዲኖር መሠረት ይጥላል።

ምዝገባው ከተጠናቀቀ በኋላ ደግሞ የዕጩዎች ክርክር የሚካሄድበት መድረክ ይዘጋጃል፤ በዚህም የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዓላማቸውንና የፖሊሲ አማራጮቻቸውን ለህዝብ በማብራራት፣ መራጩ ህዝብ በቂ መረጃ ኖሮት በትክክለኛው ግንዛቤ ላይ ተመስርቶ እንዲመርጥ ይረዳዋል።

ዋናው የምርጫ ቀን ሲደርስ ደግሞ ድምፅ የመስጠት ተግባር ይከናወናል፤ ይህም ሂደት እያንዳንዱ ዜጋ ፍላጎቱን ያለምንም ተፅዕኖ በነፃነት መግለጽ እንዲችል በሚስጥር ድምፅ የሚሰጥበት አግባብ ነው።

በመጨረሻም፣ የተሰጠው ድምፅ በግልፀኝነት ተቆጥሮ አሸናፊው የሚታወቅበት የውጤት ማሳወቅ ደረጃ ይከተላል። ይህ የመጨረሻ ምዕራፍ የህዝቡን ውሳኔ በይፋ በመቀበል ለሥልጣን ሕጋዊነትን የሚሰጥና ሉዓላዊነቱን የሚያረጋግጥበት ወሳኝ ሂደት ነው።

በአጠቃላይ፣ ምርጫ የሥልጣን ባለቤትነቱ የህዝብ መሆኑን የሚያረጋግጥ፣ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግርን የሚያሰፍንና መሪዎች ለሥራቸው ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚያደርግ ወሳኝ መሣሪያ ነው።

ይሁን እንጂ የምርጫ ጥቅም በተሟላ ሁኔታ ሊገኝ የሚችለው ሂደቱ ከምዝገባ እስከ ውጤት ማሳወቅ ድረስ ነፃ፣ ፍትሐዊና ግልጽ ሲሆን ብቻ ነው። በመሆኑም፣ እያንዳንዱ ዜጋ ይህንን መብቱን ተጠቅሞ ለሀገሩ የሚበጀውን የፖለቲካ አማራጭ በመምረጥ ረገድ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል።

የእርስዎ ድምፅ የሀገርዎን መጻኢ ዕድል የመወሰን አቅም አለውና ለመራጭነት ተመዝግበው ድምፅዎን ለሚበጅዎት የፖለቲካ ፓርቲ ለመስጠት ዝግጁ ነዎት?

ለሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ እያደረጉር ያለው ተሳትፎስ ምን ይመስላል ሃሳብዎን ያጋሩን ።

በቶለሳ መብራቴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review