AMN — መጋቢት 17/2018 ዓ.ም
በመንግሥት የሚከናወኑ የከተማ ልማትና የኢንቨስትመንት ስምሪቶች ፣ ከንግድ ትርፍ ባሻገር የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረጉ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዘርፉ የሚከናወኑ የኢንቨስትመንት ተግባራት ለማኅበረሰቡ “የወል ትርፍ” ለማስገኘት የታለሙ መሆናቸውን ገልጸው፤ ይህም የልጆችን ጤና ከመጠበቅና ተማሪዎች በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር ጀምሮ ፣ የመኖሪያ አካባቢን ሰላማዊና ጽዱ ለማድረግ ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ አብራርተዋል።
መንግሥት በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚያደርገው ጣልቃ ገብነት በዋናነት የዜጎችን የገበያ አቅም በማሳደግ የንግድ ልውውጥን ማነቃቃት ፣ መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት አጠቃላይ የኢኮኖሚ ፍሰቱ የተሳለጠ እንዲሆን ማስቻል እና ዜጎች የተሻለና የተሟላ ሕይወት እንዲመሩ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ማንኛውም ሀገራዊ የልማት እንቅስቃሴ የውጭ ሀገራትን ተሞክሮ በቀጥታ ከመቅዳት ይልቅ፣ ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታና ከሕዝቡ ነባር እሴቶች ጋር ተጣጥሞ መተግበር እንዳለበት አሳስበዋል።
በዚህ ረገድ እንደ የወንዝ ዳርቻ ልማት ያሉ ፕሮጀክቶች የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ፣ ለነዋሪዎች ምቹ፣ ማራኪና ሰላማዊ አካባቢን በመፍጠር ረገድ ያላቸው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
በበረከት ጌታቸው