AMN-ሰኔ 23/2018 ዓ.ም
የ32 ሀገራት የጥሎ ማለፍ ዙር የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ዛሬም ይቀጥላሉ። በዕለቱ ኮትዲቯር ከ ኖርዌይ ፤ ፈረንሳይ ከ ስዊድን እንዲሁም ሜክሲኮ ከ ኢኳዶር ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
ኮትዲቯር ከ ኖርዌይ
በዳላስ ስታዲየም ምሽት 2:00 የሚጀምረው ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በዓለም ዋንጫው ለአራተኛ ጊዜ እየተካፈለች የምትገኘው ኮትዲቯር ምድቧን ተሻግራ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ለማድረግ ስትዘጋጅ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ምድብ አምስትን ሁለተኛ ሆና ያጠናቀቀችው የምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ወደ ቀጣዩ ዙር የሚያሻግሯት ወጣት ባለተሰጥኦዎችን ይዛለች። ያን ዲዮማንዴ ፣ አማድ ዲያሎ ሌሎችም በዛሬው ጨዋታ ልዩነት ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከ28 ዓመት በኋላ ወደ ዓለም ዋንጫው የተመለሰችው ኖርዌይ ዛሬም በኧርሊንግ ሃላንድ ትመካለች። በፈረንሳይ በተሸነፉበት የምድብ ጨዋታ እረፍት የተሰጠው የማንችስተር ሲቲው አጥቂ በውድድሩ አራት ግቦችን አስመዝግቧል።
በተመሳሳይ በመጨረሻው ጨዋታ ላይ ያልተሳተፈው አምበሉ ማርቲን ኦዴጋርድም ይመለሳል። ሁለቱ ሀገራት ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ በታሪክ የመጀመሪያው ተብሎ ይመዘገባል።
ፈረንሳይ ከ ስዊድን

በርካቶች ዋንጫውን የማሸነፍ አቅም እንዳላት የሚመሰክሩላት ፈረንሳይ ከስዊድን ጋር ትጫወታለች። በምድብ ዘጠኝ ሦስቱንም ጨዋታዎች በማሸነፍ ያለፈችው ፈረንሳይ ያላት የተጫዋቾች ጥራት ከስዊድን አቅም በላይ ይመስላሉ።
በተለይ የኡስማን ዴምቤሌ ፣ ማይክል ኦሊሴ እና ኪሊያን ምባፔ ጥምረት ለየትኛውም ተከላካይ ፈታኝ ነው። በውድድሩ ምባፔ እና ዴምቤሌ እያንዳንዳቸው አራት ግቦችን አስቆጥረዋል።
ምድብ ስድስትን ሦስተኛ ደረጃ ይዛ ያለፈችው ስዊድን ትልቁ ተስፋዋ የአሌክሳንደር ኢዛክ እና ቪክቶር ዮኬሬሽ ጥምረት ነው። ዮኬሬሽ በምድብ ጨዋታዎች 11 ምከራ ከማድረጉም በላይ ስምንት የግብ ዕድሎችን ፈጥሯል።
አንቶኒ ኢላንጋ እና ያሲን አያሪም የስዊድን ማጥቃት አማራጮች ናቸው። ፈረንሳይ እና ስዊድን ከዚህ ቀደም በሁሉም ውድድሮች 23 ጊዜ ተገናኝተዋል። ፈረንሳይ 12ቱን ስታሸንፍ ፣ ስዊድን በስድስቱ ድል ቀንቷታል።
ሁለቱ የአውሮፓ ሀገራት ለበርካታ ጊዜ ቢገናኙም በዓለም ዋንጫ ግን የመጀመሪያቸው ነው። በኒውዮርክ ኒውጀርሲ የሚከናወነው ጨዋታ ለሊት 6:00 ላይ ይጀምራል።
ሜክሲኮ ከ ኢኳዶር
የጣምራ አዘጋጇ ሜክሲኮ በምድብ አንድ ያሳየችውን ብቃት ለመድገም ወደ ሜዳ ትገባለች። ደቡብ አፍሪካ ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ቼክ ሪፐብሊክን ምንም ግብ ሳይቆጠርባት ያሸነፈችው ሜክሲኮ ዛሬም የማሸነፍ ግምቱን ወስዳለች።
በመጨረሻ የምድብ ጨዋታዋ ጀርመንን አሸንፋ ለጥሎ ማለፍ የበቃችው ኢኳዶርም ቀላል ተጋጣሚ አትሆንም። ሜክሲኮ እና ኢኳዶር በዓለም ዋንጫው ሲገናኙ የዛሬው ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም በ2002ቱ የዓለም ዋንጫ በምድብ ተገናኝተው ሜክሲኮ 2ለ1 አሸንፋ ነበር።
የዛሬው ጨዋታ በታሪካዊው አዝቴካ ስታዲየም ለሊት 10:00 ላይ ይከናወናል።
በሸዋንግዛው ግርማ