AMN FM 96.3 ራዲዮ አዲስ የይዘትና የአቀራረብ ማሻሻያ አደረገ

You are currently viewing AMN FM 96.3 ራዲዮ አዲስ የይዘትና የአቀራረብ ማሻሻያ አደረገ

AMN- መጋቢት 25/2018 ዓ.ም

አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ኤፍኤም 96.3 ራዲዮ አዲስ የይዘትና የአቀራረብ ማሻሻያ ማድረጉን አስታውቋል።

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ኤፍ ኤም 96.3 “የትውልድ ድምፅ” በመሆን የአዲስ አበባንና የአካባቢውን ነዋሪዎች ፍላጎት መሠረት አድርጎ በተለይም ለከተማው ማህበረሰብ ዋነኛ የመረጃና የመዝናኛ ምንጭ ሆኖ እየሠራ ይገኛል። ጣቢያው የአድማጮችን ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ አዲስ የፎርማት ማሻሻያ አድርጓል።

ማሻሻያው ከዜና ሾውዎች እስከ መዝናኛና ትምህርታዊ ፕሮግራሞች ድረስ ያለውን አጠቃላይ የይዘት ፍሰት በሳይንሳዊ መንገድ ለመምራት ታቅዶ የቀረበ ነው።

የፎርማት ማሻሻያው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ኤፍ ኤም 96.3ን በኢትዮጵያ የሬዲዮ ኢንዱስትሪ ውስጥ ግንባር ቀደምና ተመራጭ ጣቢያ እንደሚያደርገው ታምኖበታል።

ፎርማቱ ከተማዋ የደረሰችበትን ደረጃ የሚያሳይና ለሁሉም የከተማው ነዋሪ የሚሆኑ ይዘቶች የተካተቱበት ሆኖ መቅረቡን የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ ተናግረዋል።

ተቋሙ በየጊዜው በተለያዩ መስኮች ራሱን እያሻሻለ መሆኑን የገለፁት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በቀጣይም ሌሎች አዳዲስ ይዘቶችን በማካተት ከጊዜው ጋር አብሮ እንደሚራመድ አረጋግጠዋል።

ኤ ኤም ኤን ኤፍ ኤም 96.3 ራዲዮ አድማጩ የሚያደምጥበት ብቻ ሳይሆን፣ የሚሳተፍበት ዘመኑን የዋጀ ሚዲያ ሆኖ መቅረቡን የገለፁት ደግሞ የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚና የራዲዮ ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ዘሃራ ሰዒድ ናቸው።

የአዲስ አበባን የሜትሮፖሊታን ትርታ የሚመጥን፣ ትውልድን የሚያንጽ እና በገበያ ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆነ ዘመናዊ የሚዲያ ተቋም ለማድረግ የተዘጋጀው ይህ ማሻሻያ፣ ጣቢያውን በመረጃ ፍሰት፣ በማህበራዊ ተፅዕኖና በገበያ መሪነት ረገድ አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍት ታምኖበታል።

በደሳለኝ መሀመድ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review