የመጋቢት ብስራት

You are currently viewing የመጋቢት ብስራት
80 Percent Discount Editable Text Effect

የተለያዩ ዕይታዎች እና መረዳት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ስልጣን መጋራታቸው ሀገርን የመገንባት ሂደት ያጠናከረ ተግባር መሆኑ ተመላክቷል

የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም ኃይላት የመጨረሻ ግባቸው ስልጣን ይዞ ያሰቡትን በተግባር ላይ ማዋል እንደሆነ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ በዓለማችን በtተለያዩ ክፍሎች የሚገኙ ፖለቲከኞችም ስልጣንን በተለያዩ መስመሮች እየጨበጡ ህዝብን በአሉታም ሆነ በአዎንታ መንገድ ሲያስተዳድሩ ማየት የተለመደ ነው፡፡

በአንዳንድ የዓለማችን ክፍል በተለይም በአፍሪካ ፖለቲካ ኃይሎች ስልጣንን በውድም በግድም ከያዙ በኋላ እንደ ነብር ጅራት ሆኖባቸው ለመልቀቅም ሆነ ለማካፈል ሲንገዳገዱ ማየት አዲስ ነገር አይደለም። በዚህም አፍሪካ በፖለቲካ ፓርቲዎች ሽኩቻ አንድ እርምጃ ወደፊት ሁለት ወደኋላ እየተጓዘች ዘመናት ነጉደዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ በአፍሪካ ፖለቲካ እና በመንግስት ስርዓቶች ላይ ባደረጓቸው የተለያዩ ጥናቶች የሚታወቁት ፈረንሳዊው የፖለቲካል ሳይንስ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ዣን-ፍራንሷ ባዋርት ‘The State in Africa’ በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ 1989 ያሳተሙትን ጥናታዊ መፅሐፍ በዋቢነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክም “የነብርን ጅራት አይዙም፤ ከያዙም አይለቁም” ይሉት አባባል ሰምሮ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስልጣንን ከያዙ አይለቁም። ለሌሎችም አያካፍሉም፡፡ በዚህም የኢትዮጵያን ከፍታ ሳይሆን የራሳቸውን ጥቅም ብቻ እያስቀደሙ ሀገርን ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም የለውጡ መንግሥት ሀገራዊ ኃላፊነትን የተረከበበት ታሪካዊ ቀን ነው፡፡ ታዲያ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ትብብርና በጋራ የመሥራት ባህል እንዲዳብር መደረጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ለአብነትም የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ ዕይታዎች፣ አሰላለፎች እና መረዳቶች ቢኖሯቸውም ለጋራ ሀገር ብሔራዊ ጥቅምን መሠረት አድርጎ በትብብር ለመሥራት ሥልጣን እስከማጋራት የተደረገው ጥረት አዲስ ፖለቲካ ባህልን ያዋለደ ተግባር ነው ሲሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሳይቀር መስክረውለታል፡፡

ለአብነትም ቢቢሲ ጥቅምት 7 ቀን 2021 ይዞት በወጣው ዘገባ “አዲስ በተመሰረተው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ካቢኔ ውስጥ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ከተቋቋመ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቃዋሚ አመራሮች በሚኒስትርነት ተሹመዋል” በማለት የነገሩን አዲስነትና ታላቅነት ዘግቧል፡፡

በወቅቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው እንዲሾሙ ካደረጓቸው 22 ሚኒስትሮች መካከል ሦስቱ በተለየ መልኩ ከተለያዩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የመጡ ናቸው። ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) የትምህርት ሚኒስትር ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፣ በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፣  የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና አቶ ቀጀላ መርዳሳ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ናቸው። ይህም ቀደም ሲል በሀገሪቱ ባልተለመደ መልኩ የተከናወነ እንደነበር የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡

ይህንንም ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት “የብልጽግና ፓርቲ አባል ባይሆኑም ሀገራቸውን በቅንነት፣ በብቃት እና በታማኝነት ማገልገል የሚችሉ ዜጎችን በካቢኔ ውስጥ የማካተት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል፡፡  በተከታታይነትም ከብልፅግና አባላት ውጭ ለሆኑ ለተለያዩ እና ብቃት እንዳላቸው ለታመነባቸው ኢትዮጵያውያን ልዩ ልዩ ሹመቶች እንደተሰጡም ይታወቃል፡፡

በወቅቱም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ባልተለመደ መልኩ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች በሚኒስትርነትና የተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ ተሹመው እያገለገሉ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በቀጣይም ተመሳሳይ ዕድሎች የሚሰጡ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ ይህ ቃል በተግባርም ተጠናክሮ መቀጠሉን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሰኔሳ ታደሰ ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት፣ በምርጫ ያሸነፈው ፓርቲ የተወሰደው እርምጃ በሀገሪቱ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ አዲስ ምዕራፍን የከፈተ ነው፡፡

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀመንበር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በወቅቱ የተሰጣቸውን ሹመት አስመልክቶ እንደተናገሩት ደግሞ፣ ከ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ውስጥ በምርጫ የሚሳተፉትን የተፎካካሪ ፓርቲዎችን በፅህፈት ቤታቸው ጋብዘው በቀጣይ አዲስ መንግስት ምስረታ ሲደረግ እስከ ዛሬ በመጣንበት መንገድ ላለመሄድ መንግስታዊ አቅጣጫ እያስቀመጠን ነው፤ በማለት ሀሳባቸውን እንዳካፈሏቸው ያስታውሳሉ፡፡ እንደ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለፃ፣ ይህንን ውሳኔ ማድነቅ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ውሳኔ አዲስ ነው፡፡ ለውጥ እንዲመጣ ይፈልጉ የነበሩ ኃይሎች ይናፍቁት ነበርም ብለዋል፡፡

ፕሬፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው፣ በወቅቱ የተሰጣቸውን ሹመት አስመልክቶ እንደገለፁት ትምህርት ሚኒስቴር ትልቅ ተቋም ነው፡፡ በመሆኑም በአዘቦት ጊዜ ከሚደረግ የፖለቲካ ፉክክር ባሻገር በዚህ ጊዜ ተባብሮ ሀገርን ለማዳን መስራት ከጤነኛ ሰው ይጠበቃል ማለታቸው አይዘነጋም፡፡

ከዚህ በፊት የፖለቲካ ባህላችን ሆኖ የቀጠለው አንድ ሰው ሚኒስትር አይደለም በቀበሌና በወረዳ ደረጃ ሕዝብን ለማገልገል ሹመት አሊያም ኃላፊነት የሚሰጠው የግድ  የፖለቲካ ፓርቲ አባል በተለይ ደግሞ ያሸነፈው የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን እንደ ግዴታ ይወሰድ እንደነበርም የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሰኔሳ አስታውሰዋል፡፡

ይህም በመሆኑ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ አገልግሎት ከመስጠት ይልቅ በስሜት፣ በግለሰብ እና በቡድን ፍላጎት ብቻ እንዲመራ ይደረግ ነበር፡፡ በዚህም በጉዳዩ ወይም በቦታው ላይ ልምድ የሌላቸው ሰዎች በስሜት እና በፈለጉት መንገድ የራሳቸውን ፍላጎት በህዝብ ላይ የሚጭኑበት ሁኔታዎች እንደነበሩ እና ይህም ሀገርን በብዙ መልኩ እንደጎዳም አውስተዋል፡፡

የዓለም ባንክ “World Development Report 2017: Governance and the Law” በሚል ርዕስ በ307 ገፅ ይፋ ያደረገው መረጃ ላይ እንዳሰፈረው ሥልጣንን የሚጋሩ የፖለቲካ ኃይላት በመካከላቸው ጤናማና ሚዛናዊ ቁጥጥርና መልካም ውድድር እንዲኖር ያደርጋሉ፡፡ የሀገራቸውን ፖለቲካዊ አስተዳደር በማሻሻል እና ሰላምን በማስፈን ኢኮኖሚያዊ ውጤት ያስገኛሉ።

የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያውም በዚህ ሀሳብ እንደሚስማሙ ገልፀው፣ አሁን ስልጣን በምርጫ በያዘው ፓርቲ አባል ያልሆኑ ሰዎች በሚኒስትር ደረጃ ተመርጠው ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት ሲሰጣቸው ይህ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያ ነው ብለዋል፡፡

የተለያዩ ዕይታዎች፣ አሰላለፎች እና መረዳቶች ያላው የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ስልጣን መጋራታቸው በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ሀገርን የመገንባት ሂደትን የሚያጠናክር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥም ጠቃሚ ያልሆኑ፣ እንደ ባህል የተወሰዱ ድርጊቶችን እና ልማዶችን የሚያስወግድ ነው፡፡ የፖለቲካ ባህላችንን ከስር መሰረቱ የሚቀይር ጥሩና የአዲስ ምዕርፍ መጀመሪያ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ለህዝብ እና ለሀገር የሚያስብ ቡድንና ግለሰብ ይህንን ያደርጋል የሚሉት የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ፣ ስልጣንን በዚህ መልኩ ማካፈል ሀገር በሁሉም ዘርፍ አሸናፊ ሆና እንድትቀጥል የሚያደርግና ኢትዮጵያን የፖለቲካ ባህል የሚቀይር እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሰኔሳ ታደሰ ልምድና እውቀት ላላቸው ሰዎች ይህን መሰል ዕድል መስጠት እንደ ሀገር ትልቅ ጥቅም ያለውና የፖለቲካ ፓርቲዎችም ትምህርት ሊወስዱበት የሚገባ ነው ብለዋል፡፡

አክለውም ይህንን መሰል አሰራር በሌሎች ዓለማትም ያለ በመሆኑ ዘመኑ ከደረሰበት ስልጣኔ ጋር አብረን መጓዝ አለብን፡፡ ፖለቲካ ፓርቲዎችም ይህንን እውነት መቀበል አለባቸው፡፡ ምክንያቱም አንድ ፖለቲካ ፓርቲ ሲመሰረት ስልጣን ይዜ ሀገሬን እና ህዝቤን አገለግላለሁ፤ ሀሳቤን እና ፍላጎቴን አራምዳለሁ ብሎ ነው፡፡

ታዲያ ይህን ብሎ ወደ ስልጣን የመጣው ፓርቲ  ሀገር እንድታሸንፍ የእኔ አባላት ባይሆኑም የተሻለ ብቃት ስላላቸው በሚል መስፈርት ስልጣኑን ሲያካፍል ግለሰቦችም በተሰጣቸው ዕድል ህዝባቸውን ማገልገል እና በመካከላቸውም ለአንድ ሀገር እንደሚያስቡ ህዝቦች መተያየት አለባቸው፡፡

አክለውም ኢትዮጵያ እንደ ዘመናዊ ሀገር ከተመሰረተችበት ጊዜ አንስቶ ባለው ታሪክ ስልጣን ከአንዱ ወደ አንዱ የሚሸጋገረው በዚህ መልኩ አልነበረም። በተለይ ለአንድ ሀገር እንደሚሰራ ሳይሆን እንደ ጠላት የሚተያዩበት ነበር፡፡ አሁን ግን ተፎካካሪ የምንላቸው ኃይሎች ስልጣንን በዚህ መልኩ ሲያካፍሉ በታሪካችን ያየናቸው የግጭት አዙሪቶች እየተቀረፉ እንደሚሄዱም አመላክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ስልጣን በተጋራበት ወቅት ለምክር ቤቱ አባላት ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያ ፖለቲካ እሳቤ ያላቸው ሰዎች የሚሰደዱበት፣ የሚጣሉ እና አሸናፊ ብቻ የሚገዛበት ሁኔታ መቀየር አለበት ካልን ይህ ትልቅ ነገር ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡

 በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review