የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ምክንያታዊ ነው -የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባል

You are currently viewing የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ምክንያታዊ ነው -የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባል

‎AMN-መጋቢት 29/2018 ዓ.ም

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ ከአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባል ቲዬሪ ማሪያኒ ጋር በሀገራዊና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሂዷል።

‎የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ የባህር በር ማጣቷን ገልፀው፤ በአሁኑ ወቅት እያስመዘገበችው ካለው የኢኮኖሚ እና የሕዝብ ቁጥር ዕድገት አንጻር የራሷ የባህር በር መኖር ጉዳይ ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።

‎ኢትዮጵያ ይህንን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ እና በስምምነት ለመፍታት ጥረት እያደረገች መሆኑንና ጎረቤት አገራትም ለዚህ አዎንታዊ ምላሽ እንደሚሰጡ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

‎የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባል ቲዬሪ ማሪያኒ እንደገለፁት፤ የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄ ወቅታዊ፣ ታሪካዊ እና በምክንያት ላይ የተመሰረተ ነው ብለዋል።

‎ኢትዮጵያ ያቀረበችው የባህር በር ጥያቄ ተገቢ መሆኑን ያመላከቱት የህብረቱ ፓርላማ አባል፤ ጉዳዩ ለቀጠናው የጋራ ዕድገት ፋይዳው የጎላ መሆኑንም አስረድተዋል።

‎በ1950ዎቹ በተባበሩት መንግሥታት የነበረውን የታሪክ ሂደትን ያስታወሱት ቲዬሪ ማሪያኒ፣ የኢትዮጵያን ፍላጎት ለማሳካት አስፈላጊውን ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በውይይቱ የታላቁ የህዳሴ ግድብ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ ምንም ዓይነት የውኃ መቀነስ አለማስከተሉን በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ዝግጅት ካለምንም ችግር እንዲጠናቀቅ መንግስት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ሰብሳቢው አብራርተዋል፡፡

‎የውይይት መድረኩ በአውሮፓ ፓርላማ እና በኢትዮጵያ ፓርላማ እንዲሁም በፈረንሳይ እና በኢትዮጵያ ፓርላማ መካከል ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑንም ሰብሳቢው ማመላከታቸዉን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review