AMN-መጋቢት 30/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ አሁን ያሉትን 100 በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ቬሎሲቲ የአዉቶቡሶች ቁጥርን በሚቀጥሉት በሶስት አመታት ወደ 500 ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን አስታዉቋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ በመንግስት እና በግል አጋርነት አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው ቬሎሲቲ ትራንስፖርት የተመሰረተበትን አንደኛ ዓመት በማስመልከት ማብራሪያ ሰጥቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ያብባል አዲስ ድርጅቱ 100 አውቶቡሶችን ይዞ አገልግሎት በሰጠበት ባለፈው አንድ አመት ብቻ 40 ሚሊዮን ተጓዦችን ማጓጓዝ መቻሉን ገልጸዋል፡
በዚህም ከከተማዋ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ውስጥ የብዙኅን ትራንስፖርት ድርሻ ከ36 በመቶ ወደ 42 በመቶ ማደግ ችሏል ብለዋል።
በመንግስትና በግል አጋርነት አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው ቬሎሲቲ ትራንስፖርት የስምሪት፣ የክፍያ እና የቁጥጥር ስርዓቱን በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን ስለማድረጉም ኃላፊው ገልጸዋል።

አሁን ላይ ያሉትን 100 የአውቶቡሶች ቁጥር በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ውስጥ ወደ 500 ለማሳደግ እየተሰራ ነውም ተብሏል።
ቬሎሲቲ ትራንስፖርት ለ500 ዜጎች የስራ ዕድል ስለመፍጠሩም ተገልጿል።
ለቬሎሲቲ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ዴፖ የሚገነባ መሆኑን ያስታወቁት አቶ ያብባል አዲስ፤ የግንባታ ቦታ የማመቻቸት ስራውን መንግስት እያከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በበላይሁን ፍስሃ