AMN – ሚያዝያ 6/2018 ዓ.ም
በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢንዱስትሪው ዘርፍ እየታዩ ያሉ መሠረታዊ ለውጦችና የኃይል አጠቃቀም አዝማሚያዎች፣ ታዳሽ ኃይልን ለምትጠቀመው ኢትዮጵያ ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድል ይዘው መምጣታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢቢሲ በሰጡት ማብራሪያ፤ የዓለም የኢንዱስትሪ ሽግግር አቅጣጫውን ወደ ንጹህ ኃይል ማዞሩ ለሀገሪቱ አዲስ የውድድር ብልጫ እንደሚሰጣት ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በዓለም ገበያ ላይ አንድ ምርት ተፈላጊ የሚሆነው በጥራትና በዋጋው ብቻ ሳይሆን፣ ለምርቱ ሂደት በዋለው የኃይል ምንጭ ጭምር መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በተለይም በታዳሽ ኃይል የሚመረቱ እንደ አሉሚኒየም ያሉ ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያላቸው በመሆኑ፣ ሙሉ በሙሉ (100%) ታዳሽ ኃይል የምትጠቀመው ኢትዮጵያ የብዙ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የትኩረት ማዕከል ሆናለች።
በአሁኑ ወቅትም አምስት የሚጠጉ ግዙፍ ኩባንያዎች በአሉሚኒየም ማምረቻ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

የአሉሚኒየም ማምረቻ ፋብሪካዎች ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት ያላቸው መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አንድ ፋብሪካ እስከ 800 ሜጋ ዋት ኃይል ሊጠይቅ እንደሚችል አስረድተዋል።
ይህም ከሀገሪቱ የኃይል አቅርቦት አቅም አንጻር ከፍተኛ ድርሻ የሚወስድ በመሆኑ፣ ኢንቨስትመንቱን ከኃይል አቅርቦቱ ጋር በማመጣጠን ረገድ ጥንቃቄ የተሞላበት አመራር እየተሰጠ መሆኑን አብራርተዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የገነባቻቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሙሉ ታዳሽ ኃይልን መሠረት ያደረጉና የዜሮ ፍሳሽ ማጣሪያ ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙ በመሆናቸው፣ በአካባቢ ጥበቃ ረገድ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን የሚያሟሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይህም ሀገሪቱ ከካርቦን ነፃ የሆነ የኢንዱስትሪ ልማትን ለመገንባት ለያዘችው ግብ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
በበረከት ጌታቸው