AMN – ሰኔ 14/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ የዳታ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባለፈ፣ በሀገር ውስጥ የሃርድዌር ምርቶችን በማምረት ወደ ሙሉ የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት ለመሸጋገር የሚያስችል ታሪካዊ መሰረት እየጣለች መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ”ዲጂታል ለልህቀት” በሚል መሪ ሀሳብ በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀውን የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ የሪፎርም ውጤቶችን ማሳያ ኤግዚቢሽን መርቀው በከፈቱበት ወቅት እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ላፕቶፕና አይፓዶችን ለማምረት የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
የዳታ እና የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት ያላቸውን መዋቅራዊ ልዩነት እንዲሁም ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የያዘችውን ስትራቴጂካዊ አቅጣጫ በዝርዝር አብራርተዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ማብራሪያ፣ ወደ ሙሉ የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት ከመደረሱ በፊት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በዘርፉ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የዳታ ሉዓላዊነትን ማስከበር ቀዳሚው ምዕራፍ ነው።

ዳታ የአንድ ሀገር ውድ ሀብት በመሆኑ የዳታ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጥ አሰራር መዘርጋት ቀዳሚ ተግባር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህንን ስትራቴጂ በርካታ ሀገራት ስኬታማ እንዳደረጉት ሁሉ ኢትዮጵያም እንደምታሳካው እርግጠኛ ነኝ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የዳታ ደህንነት እና ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በካቢኔ ደረጃ ህግ ከማውጣትና በብሔራዊ የክላውድ ግንባታ በተቋማት ደረጃ ስራዎችን ከመጀመር ባለፈ፣ ሂደቱን በሀገር ውስጥ የሃርድዌር ምርት መደገፍ የግድ አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የሀገሪቱን የቴክኖሎጂ አቅም ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሰው ሰራሽ አስተውሎ (AI) ኢንስቲትዩት እና ከኤአይ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በሀገር ውስጥ የላፕቶፕ እና የአይፓድ ምርትን ለመጀመር ወደ ሥራ መግባቱን ጠቁመዋል።
ይህ የተቀናጀ ጥረት በጥቂት ዓመታት ውስጥ በሶፍትዌርና በዳታ ላይ ያለውን ብቃት ወደ ሃርድዌር ደረጃ በማሸጋገር፣ የነገዋን ኢትዮጵያ ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግራት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

በሶፍትዌር ረገድ የተመዘገበው ብቃት ሀገሪቱ የዳታ ሉዓላዊነትን እንድታልምና እንድትተገብር የረዳት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሃርድዌር ደረጃ የተጀመሩት የማምረት ስራዎች እያደጉ ሄደው ከጥቂት ዓመታት በኋላ የሚመጣው አዲስ ትውልድ ሙሉ የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነትን ለማወጅ የሚያስችለውን ጠንካራ አቅምና መሰረት የሚጥል እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።
በበረከት ጌታቸው