AMN — ሚያዝያ 07/2018 ዓ.ም
የላይቤሪያ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት ጆሴፍ ንዩማ ቦአካይን በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት እና በሁለቱ አገራት መካከል የተደረጉት ስምምነቶች ለወደፊት ትብብር እንደ ስትራቴጂካዊ መሠረት እና ተግባራዊ ፍኖተ-ካርታ የሚያገለግሉ ናቸዉ፡፡
ምንም እንኳን የአገራቱ ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እ.አ.አ በ1958 የተጀመረ ቢሆንም፣ ጥምረታቸው ግን ከዚያ ቀደም ብሎ በቅኝ አገዛዝ ዘመን ለአፍሪካ ነፃነትና ለፓን-አፍሪካኒዝም በጋራ በመቆም የጠነከረ ነው።
ዛሬ ላይ ይህ ታሪካዊ ወዳጅነት በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና በተለያዩ በልማት ዘርፎች እየታደሰ ይገኛል።
ፕሬዝደንት ጆሴፍ ንዩማ ቦአካይን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር ባደረጉት ፍሬያማ የሁለትዮሽ ውይይት በሀገራቱ መካከል ያለውን የቆየ አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

በዚህም አገራቱ ትብብራቸውን ስትራቴጂካዊ መሠረት የሚያስይዙ ሁለት የመግባቢያ ስምምነቶች ተፈራርመዋል።
ስምምነቶቹ በትምህርት ፣በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በፈጣን የለውጥ ጉዞ ያካበተችውን ልምድና ሰፊ ዐቅም ለላይቤሪያና ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ለማካፈል ዝግጁ ናት።
ይህ ትብብር ኢትዮጵያ እና ላይቤሪያን በመደመር መርህ በማጣመር ለአህጉራዊ ትስስር ዋነኛ አንቀሳቃሽ ኃይል ከመሆኑም ባለፈ፣ የአፍሪካ አገራት በእውነተኛ ትብብር ምን ሊያሳኩ እንደሚችሉ እንደ ትልቅ ተምሳሌት የሚጠቀስ ይሆናል።
በትዝታ መንግስቱ