AMN- ሚያዝያ 7/2018 ዓ.ም
የሀገሪቱን የኢንዱስትሪ ሽግግር ለማፋጠን የተነደፈው ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገበ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የሉዓላዊነት ልብ” በሚል ርዕስ ኢትዮጵያ ውስጥ ይመረት እና ኢትዮጵያ ታምርት የሚሉት እሳቤዎች የተለያዩ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ይመረት የሚለው እሳቤ ባለሀብቶች ከየትም መጥተው በሀገሪቱ ውስጥ እንዲያመርቱ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ታምርት ደግሞ ኢትዮጵያውያን በስፋት ወደ ምርት ዘርፍ ገብተው የሀገርን ኢኮኖሚ እንዲደግፉና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችል የንቅናቄ እሳቤ መሆኑን አስረድተዋል።
በንቅናቄው በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከመንግስት መር ወደ ግሉ ዘርፍ በተደረገው የኢኮኖሚ ሽግግር፣ በለውጡ መጀመሪያ 8 ሺህ ገደማ የነበሩ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች በአሁኑ ወቅት ወደ 26 ሺህ አድገዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ አቁመው የነበሩ ከ8 መቶ በላይ ፋብሪካዎችም ችግራቸው ተፈቶ ዳግም ወደ ምርት እንዲመለሱ ተደርጓል ብለዋል።
ለኢንዱስትሪዎች የሚቀርበው የኃይል አቅርቦት ያደገ ሲሆን፣ የቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትም ወደ 22 በመቶ ደርሷል ነው ያሉት።
ቀደም ሲል ከውጭ ይገቡ የነበሩ አንዳንድ ምርቶችንም መቶ በመቶ ማስቀረት እንደተቻለና ይህም በሚሊየን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሬን ማዳን እንዳስቻለ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ንቅናቄው ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ጥቂት ዓመታት ቢሆነውም፣ የሀገሪቱን የኢንዱስትሪ መዋቅር በመቀየርና የገበያ ስርዓቱን በማዘመን ረገድ አስገራሚ ውጤት እያመጣ መሆኑን በዝርዝር አብራርተዋል።
በአስማረ መኮንን