በ9 ወራት ውስጥ 50 ሺህ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ከሸፉ

You are currently viewing በ9 ወራት ውስጥ 50 ሺህ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ከሸፉ

AMN-ሚያዚያ 21/2018 ዓ.ም

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በ9 ወራት የተሰነዘሩ ከ50 ሺህ በላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎችን በማክሸፍ የዲጂታል ሉዓላዊነትን የማስጠበቅ ስራውን በብቃት እየተወጣ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ ገለጹ።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የ2018 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ገምግሟል።

የ”ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030″ ስትራቴጂያዊ ራዕይ ከማሳካት፣ ብሔራዊ ደህንነትን ከማረጋገጥ እንዲሁም ኢትዮጵያ በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ያላትን ቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ይበልጥ ከማሳደግ አኳያ አፈጻጸሙ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑ በግምገማው ተገልጿል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሀገሪቱ ቁልፍ መሰረተ-ልማቶችና ተቋማት ላይ 50ሺህ 155 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች የተሰነዘሩ ሲሆን ፤ ከዚህ መካከል ሰርጎ ገብ ጥቃት በ20ሺህ 601 የጥቃት ሙከራዎች ከፍተኛውን ወይም 41% በመቶ እንደሚሸፍን ተገልጿል።

አስተዳደሩ ባደረገው የነቃ የ24 ሰዓት ክትትልና በዘረጋው የላቀ የመከላከያ አቅም ከእነዚህ ጥቃቶች ውስጥ 99 በመቶ የሚያህሉትን ሙሉ በሙሉ ማክሸፍ መቻሉ ነው የተገለጸው።

ዋና ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ፣ ተቋሙ 99 በመቶ ያህሉን የጥቃት ሙከራ ማክሸፍ መቻሉ የአስተዳደሩን ኦፕሬሽናል ልህቀት የሚያሳይ ነው።

የሀገሪቱን የዲጂታል ሉዓላዊነት በጽኑ መሰረት ላይ ለማቆም ግዙፍ መሰረተ-ልማቶችን በመገንባትና በማስፋፋት ረገድ ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውንም ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

የሀገሪቱን የዲጂታል ሽግግር በራስ አቅም ለመምራትና የውጭ ጥገኝነትን ለመቀነስ፣ ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ ምርቶችን እና መፍትሄዎችን የማልማትና ለተለያዩ ተቋማት የማስታጠቅ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተጠቅሷል።

አስተዳደሩ ከሙስና፣ ከማጭበርበር እና ከማህበራዊ ሚዲያ ጋር የተያያዙ 5ሺህ 604 የፍራውድ መከላከል ስራዎችን በማከናወን በዜጎችና በተቋማት ላይ ሊደርስ የነበረውን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ቀውስ አስቀድሞ መከላከል ችሏል ተብሏል።

የሳይበር ደህንነት የቴክኖሎጂ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሀገራዊ ሉዓላዊነትና የብሔራዊ ደህንነት ዋስትና መሆኑን ዋና ዳይሬክተሯ ጠቁመው፤ ኢመደአ አስተማማኝና የማይበገር የሳይበር ምህዳር ለመፍጠር በቁርጠኝነት መስራቱን ይቀጥላል መለታቸውን ከኢመደአ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review