AMN- ሚያዝያ 24/2018 ዓ.ም
ሴቶች በሀገር ግንባታ ውስጥ ያበረከቱትና እያበረከቱት ያለውን አስተዋጽኦ የሚዳስስ “ሴቶችና የሀገር ግንባታ” በሚል መጽሀፍ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ምሁራን በተገኙበት በኦሮሞ ባህል ማዕከል ተመርቋል።
ሴቶች ከቤተሰብ አልፈው የማህበረሰብ ብሎም የሀገር ምሰሶ ናቸው ያሉት የቀድሞ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት እና የዲቦራ ፋውንዴሽን መስራች አቶ አባ ዱላ ገመዳ በሀገር ግንባታ ውስጥ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ለትውልድ ማስተዋወቅና ሰንዶ ማስቀመጥ ይገባል ብለዋል።
መጽሀፉ ሴቶች በሀገር ግንባታ ውስጥ እየተጫወቱ ያለውን ሚና የሚያሳይ መሆኑን አንስተው ይህም ለቀጣዩ ትውልድ ትልቅ መነቃቃትን የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ትውልዱ አሁን ላይ እንደ ሀገር ለሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ የተሠጠውን ልዩ ትኩረት በመጠቀም የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ማንቃት የመጽሀፉ ዓላማ መሆኑን ጸኃፊዋ ሊዲያ ከድር ተናግረዋል።

መጽሀፉ ሴቶች ለሀገር ግንባታ ለሚያበረክቱት አስተዋጽኦ መንገድ ከመጠቆም ባለፈ አርአያ የሆኑ ሴቶችን ተሞክሮ የተዳሰሰበት መሆኑንም አንስተዋል።
መንግስት ለሴቶች የሰጠውን ትኩረት ተጠቅመው ለሀገር ግንባታ የሚያዋጡትን አስተዋጽኦ እንዲያጠናክሩ የሚያግዝና ለፖሊሲ አውጪዎች ግብአት እንደሚሆን በምረቃ ስነ-ስርዓቱ የተገኙ ታዳሚዎች ተናግረዋል።
መጽሃፉ በአፋን ኦሮሞና በአማርኛ ቋንቋ የተጻፈ ሲሆን አሁን ላይ በኦሮሞ ባህል ማዕከል እንደሚገኝና ከጥቂት ጊዚያት በኋላ በሶፍት ኮፒ እንደሚቀርብ ተመላክቷል።
በሔኖክ ዘነበ