AMN- ሚያዚያ 30/2018 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ጋር በነበራቸው ቆይታ ሚዲያዎች ከሴራ ትንተና ወጥተው በእውነትና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ሚዛናዊ ዘገባ ሊያቀርቡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመንግስትና በግል ሚዲያዎች መካከል ያለውን የመንግስትና የንግድ ፍላጎት የሚሉ ጎጂ አመለካከቶችን ለመስበር ሚዛናዊነት ብቸኛው መፍትሄ መሆኑን ገልጸዋል።
በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ ክፍተቶችን በሚመለከት በሰጡት ማብራሪያም፤ “በውስጣችን ሌቦች፣ ጥፋተኞች፣ የማይሰሩና ሁሉም አይነት ስብስብ አሉ” በማለት ሚዲያዎች ጥፋቶችን በበቂ መረጃና ትንተና ሊያጋልጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ሚዲያዎች በደፈናው አርዕስተ ዜና ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ በመረጃ የተደገፈ ጥልቅ ትንተና ማቅረብ እንዳለባቸው በማንሳት መንግስት የሚሰራቸውን ስህተቶች በመረጃ ለሚጠቁሙ ሚዲያዎች ምላሽ ለመስጠትና ለማስተካከል ዝግጁ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር)፤ በሀገሪቱ የሚሰሩ አበረታች የልማት ስራዎች እንዳይዳፈኑ እና እንዲታወቁ ሚዲያዎች ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በተለይም እንደ “ኪንግስ ኦፍ አባይ” ያሉ የሚዲያ ተሞክሮዎች በሀገር ወዳድነትና በእውነት ላይ ተመስርተው የሚሰሩትን ስራ በምሳሌነት አንስተዋል።
የክልል ሚዲያዎች ድጋፍን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ የፌዴራል መንግስት የፌዴራል ተቋማትን እንደሚደግፈው ሁሉ ክልሎችም የራሳቸውን የሚዲያ ተቋማት የማጠናከር ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) “የሚዲያ እመርታ ለትርክት ግንባታ” በሚል መሪ ሀሳብ ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ባደረጉት ውይይት በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ስራዎቻቸውን በዕውቀት፣ በምርምርና እውነት ላይ በመመስረት ለሀገር ግንባታና ለህዝብ ጥቅም የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በትዝታ መንግስቱ