AMN ግንቦት 5/2018
ፖሊሲዎች የወረቀት ሰነድ ብቻ ሳይሆኑ የዜጎችን ሕይወት የሚቀርጹ ተግባራዊ መሣሪያዎች ናቸው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በመልዕክታቸው ውጤታማ ፖሊሲ ለሀገራዊ ዕድገት የጀርባ አጥንት ነው ብለዋል።
ዛሬ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከበረው የፖሊሲ ቀን ፖሊሲ ለሕዝብ ጥቅም እና ለሀገር የነገ መዳረሻ የሚታለምበት የቃል ኪዳን ሰነድ መሆኑን የምናምንበት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
መንግሥት በግልፅ፣ ተተግባሪና ጥራት ባላቸው ፖሊሲዎቹ አማካኝነት ለሕዝብ የገባውን ቃል በተግባር እየተረጎመ ስኬቶችን እያስመዘገበ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የበለጸገ ሀገር የሚገነባው በተጨባጭ መረጃ በተደገፈ ጥናትና ፖሊሲዎችን ከዓለም አቀፋዊ እውነት ጋር በማስማማት መሆኑን ጠቅሰው፤ የመንግሥት ውሳኔ አሠጣጥ በማስረጃ ላይ ሲመሠረት ይበልጥ የሠመረ እንደሚሆን አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና በፍጥነትና በፈጠራ ለማሳካት የፖሊሲ ትንተና እና አወቃቀር ሙሉ በሙሉ በምርምርና በማስረጃ ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።
ፖሊሲዎች የወረቀት ሰነድ ብቻ ሳይሆኑ የዜጎችን ሕይወት የሚቀርጹ ተግባራዊ መሣሪያዎች መሆናቸውንም አክለዋል።
እንደ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ያሉ ተቋማት በምርምርና በተግባራዊ ውሳኔዎች መካከል ድልድይ በመሆን የልማቱ የጀርባ አጥንት ሆነው እያገለገሉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ በምትገኝበት በዚህ ወቅት፣ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ በጂኦ-ፖለቲካዊና በቴክኖሎጂ ለውጦች ላይ ቀድሞ ምላሽ የሚሰጡ ጥናቶች እንደሚያስፈልጉ ጠቁመው፤ ለዚህም የፖሊሲ ተመራማሪዎች ከመፍትሔ አመንጪነት እስከ ትግበራ ሀሳብ ድረስ የላቀ ሚና እንዳላቸው አመልክተዋል።
መንግሥት በዕውቀት ላይ ኢንቨስት በማድረግ እና ለማስረጃዎች ዋጋ በመስጠት፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆነ የፖሊሲ ሥነ-ምህዳር ለመገንባት ቁርጠኛ መሆኑን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለዚህ ስኬት ሁሉም በጋራ እንዲሠራ አሳስበዋል።