AMN- ግንቦት 6/2018 ዓ.ም
ቋቁቻ በብዙዎቻችን ዘንድ የሚታወቅና በተለይም በሞቃታማ የአየር ጸባይ ወቅት ጎልቶ የሚወጣ የቆዳ ችግር ነው።
ብዙዎች ይህን ችግር ከለምጽ ወይም ከሌሎች የቆዳ በሽታዎች ጋር ሲያመሳስሉት ይታያል። የቆዳና የአባላዘር ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር መለሰ ጡሚሶ ከ ኤ ኤም ጋር በነበራቸው ቆይታ ስለ ቋቁቻ መንስኤ፣ መከላከያ መንገዶችና ህክምና ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ቋቁቻ ምንድን ነው?
ቋቁቻ በቆዳችን ላይ ክብ እየሰሩ የሚወጡ፣ አብዛኛው ጊዜ ነጣ ያሉ፣ አልፎ አልፎ ደግሞ ጠቆር ብለው ወደ ቡናማነት የሚያደሉ ነጠብጣቦች ናቸው። ይህ የቆዳ ችግር በብዛት የሚወጣው፣ ፊት ላይ፣ ደረት አካባቢ፣ አንገት ላይ እና፣ ጀርባ ላይ ነው።
የቋቁቻ መንስኤ ምንድን ነው?
የቋቁቻ መንስኤ ማላሴዚያ ፉርፉር (Malassezia furfur) የተባለ የፈንገስ አይነት ነው። ይህ ፈንገስ በአብዛኛው ሰው ቆዳ ላይ በጤነኛ ሁኔታ የሚኖር ቢሆንም፣ ምቹ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ግን ከሚገባው በላይ በማደግ የቆዳ ችግር ያስከትላል።
ለፈንገሱ እድገት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ ነገሮች፣ የቆዳ ስብ ወይም ወዝ መጨመር ሲሆን ይህም የቆዳ ቅባት መብዛት ለፈንገሱ እድገት ምግብ ይሆናል። ከመጠን በላይ የሆነ ላብ እርጥበትና ሙቀት ፈንገሱ እንዲራባ ያደርጋል።
የሰውነት በሽታ የመከላከል አቅም መዳከም ለምሳሌ የስኳር ህመም ያለባቸው ሰዎች ለዚህ ተጋላጭ ናቸው። አንዳንድ ቤተሰቦች በተፈጥሮአቸው ለቋቁቻ ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ።
ቋቁቻ ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል?
ይህ ትልቅ ግንዛቤ ሊያዝበት የሚገባ ነጥብ ነው። ቋቁቻ ከሰው ወደ ሰው በንክኪ ወይም ልብስ በመቀያየር አይተላለፍም።
ፈንገሱ በሁሉም ሰው ቆዳ ላይ የሚገኝ በመሆኑ፣ ህመሙ የሚከሰተው ፈንገሱ በራሳችን ቆዳ ላይ ምቹ ሁኔታ አግኝቶ ሲያድግ ብቻ ነው።
ቋቁቻን ከለምጽና ከፎረፎር እንዴት እንለየዋለን?
ለምጽ የቆዳ ቀለም ፍጹም ነጭ ሆኖ የሚጠፋበትና ምንም አይነት ብናኝ (ቅርፊት) የሌለው ነው። ቋቁቻ ግን ነጣ ያሉ ብናኞች አሉት፤ በተለይ ከሻወር በኋላ ወይም ቆዳውን ፋቅፋቅ ስናደርገው የሚቀረፋ ቅርፊት ይታይበታል።
ፎረፎር አብዛኛውን ጊዜ የሚወጣው ፊት ላይ በተለይ አፍንጫ ስር እና ራስ ቅል ላይ ሲሆን፣ ቅርፊቶቹም ግግር የማለት ባህሪ አላቸው።
መከላከያ መንገዶች
ቋቁቻ እንዳይከሰት ወይም ተመልሶ እንዳይመጣ በተለይ የሚያልበን ከሆነ ቶሎ ቶሎ መታጠብ ንጽህናን መጠበቅ፣ ወዛማ ቆዳ ያላቸው ሰዎች ተጨማሪ ቅባቶችን ባይጠቀሙ ይመረጣል።
የስኳር ህመም ያለባቸው ሰዎች የስኳር መጠናቸውን በአግባቡ መቆጣጠር ይኖርባቸዋል።
ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች በሳምንት አንድ ቀን የጸረ-ፈንገስ ሻምፖዎችን ለሰውነት መታጠቢያነት መጠቀም ይችላሉ።
ህክምናው
ቋቁቻ ሙሉ በሙሉ መዳን የሚችል የቆዳ ችግር ነው። እንደ መጠኑና እንደ ስፋቱ ችግሩ ውስን ቦታ ላይ ብቻ ከሆነ የሚቀቡ መድሃኒቶች፣ ቋቁቻው ሰፋ ያለ ቦታ ላይ ከወጣ፣የጸረ-ፈንገስ ሻምፖዎች ይታዘዛል፡፡
ችግሩ በጣም ሰፊ በሚሆንበት ጊዜ በሀኪም ትእዛዝ የሚወሰዱ የሚዋጡ መድሃኒቶች ሊሰጡ ይችላሉ፡፡
ቋቁቻ ህክምና አለው ስለዚህ ምልክቶቹ ሲታዩ ወደ ቆዳ ሀኪም በመሄድ ተገቢውን ምርመራና ህክምና እንዲያገኙ ዶክተር መለሰ ይመክራሉ።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ