የብሪክስ አባል ሐገራት ሁሉን አቀፍ የዓለም ሥርዓት ለመገንባት በጋራ ይሰራሉ-የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ

You are currently viewing የብሪክስ አባል ሐገራት ሁሉን አቀፍ የዓለም ሥርዓት ለመገንባት በጋራ ይሰራሉ-የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ

AMN-ግንቦት 6/2018 ዓ.ም

የብሪክስ አባል ሐገራት ዘላቂ ልማትን ለማበረታታት፣ ኢኮኖሚያዊ ጽናትን ለማሳደግ እና ሁሉን አቀፍ የዓለም ሥርዓት ለመገንባት በጋራ እንደሚሰሩ የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ገለጹ፡፡

በህንድ ኒው ዴልሂ ለሁለት ቀናት የሚቆየው የብሪክስ አባል ሃገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ስብሰባውን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት ከብሪክስ አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና ከልዑካን መሪዎች ጋር የተደረገው ግንኙነት አስደሳችና ጠቃሚ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ብሪክስ በታዳጊ ኢኮኖሚዎች መካከል ትብብርን ለማጠናከር እና የግሎባል ሳውዝ ሃገራት ፍላጎቶችና ድምፆች እንዲሰሙ አስፈላጊ መድረክ ሆኖ መገኘቱን ተጠቅሷል።

አባል ሃገራቱ ዓለም አቀፍ ተቋማዊ ትብብርን ለማጠናከር፣ ዘላቂ ልማትን ለማበረታታት፣ ኢኮኖሚያዊ ጽናትን ለማሳደግ እና ሁሉን አቀፍ የዓለም ሥርዓት ለመገንባት በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በስብሰባዉ ላይ በመሳተፍ ላይ የሚገኙ ሲሆን ከስብሰባው ጎን ለጎን ከህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋር ተገናኝተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር ሁሉንም ሀገራት በፍትሃዊነት የሚያገለግል ዓለም አቀፍ ስርዓት ለመገንባት የተቀናጀ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ አስፈላጊነትን አጽንኦት ሰጥተውበታል።

አሁን ያለው ዓለም አቀፋዊ ቀውስ በአስቸኳይ ካልተፈታ በሀገራት ድንበር ብቻ ሊገታ የማይችል ከፍተኛ የኢኮኖሚ፣ የፋይናንስ እና የማህበራዊ አለመረጋጋት መዘዞችን እንደሚያስከትልም አስገንዝበዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከደቡብ አፍሪካው የዓለም አቀፍ ግንኙነትና ትብብር ሚኒስትር ሮናልድ ላሞላ ጋርም በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

ውይይቱ በሀገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ያተኮረ ሲሆን ሚኒስትሮቹ በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሱ ያሉ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት መስማማታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

ህንድ በዚህ ዓመት የህብረቱ ሰብሳቢ ሆና በማገልገል ላይ የምትገኝ ሲሆን ጉባኤዉም “ፅናት ፣ ፈጠራ ፣ ትብብርን እና ዘላቂነትን መገንባት” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ይገኛል።

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review