የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ዕምብርት የሆነችው አዲስ አበባ የቱሪዝም የስበት ማዕከል እየሆነች ነው

AMN – ነሐሴ 10/2018 ዓ.ም

የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ባከናወነችው መጠነ ሰፊ የኮሪደር፣ የወንዝ ዳርቻ ልማት እና የመልሶ ግንባታ ሥራዎች ማራኪ ገጽታን ተላብሳለች።

ቀደም ሲል ለቆሻሻ መጣያነት እና ለወንጀለኞች መሸሸጊያነት ተጋልጠው የነበሩት የወንዝ ዳርቻዎች ከብክለት ጸድተው፣ ውብና ማራኪ በመሆናቸው ለሕዝብ ማረፊያና መዝናኛነት የሚመቹ ሆነዋል።

በተጨማሪም ከአካባቢ ብክለት ጋር ተያይዞ ይከሰቱ የነበሩ በሽታዎችን መከላከል የተቻለ ሲሆን፤ በከተማዋ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት እና የሥራ ዕድል እየተፈጠረ ይገኛል።

የለውጡ ማሳያ የሆኑት ዋና ዋና አውራ ጎዳናዎች፣ የብስክሌት መንገዶች፣ ሰፊና ንጹህ የእግረኛ መንገዶች እንዲሁም የፍሳሽ ማስወገጃዎች ከተማዋን ከነበረችበት የቆየ የአኗኗር ዘይቤ በማላቀቅ ለዘመናዊ ኑሮ ምቹ አድርገዋታል።

በተከናወኑት ተጨባጭ የልማት ሥራዎችም በጸሐይ ኃይል የሚሠሩ የጎዳና ላይ መብራቶች፣ ዘመናዊ የትራፊክ መቆጣጠሪያዎች እና የተሽከርካሪ መቆሚያዎች በየአካባቢው ተዘርግተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ለነዋሪዎችና ለጎብኝዎች የሚመጥኑ ዘመናዊ መኖሪያዎችና አገልግሎት መስጫዎች የተገነቡ ሲሆን፣ ሙዚየሞች፣ ፓርኮች፣ ታሪካዊ ቅርሶች እና የባህል ማዕከላት ነባሮቹን በማደስና አዳዲስ ግንባታዎችን በማከናወን የከተማዋን መልክ እንዲቀየር አድርገውታል።

ከተማዋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ለኑሮ ምቹ እየሆነች መምጣቷን ተከትሎም፣ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ሀገር ጎብኝዎችን ቀልብ እየሳበች ትገኛለች።

የአዲስ አበባ ቱሪዝም መረጃ እንደሚያመላክተው አሁን ላይ መዲናዋ ለቱሪስቶች ረዘም ላለ ቀናት መቆየት የሚያስችሉ በርካታ አማራጮች ያሏትና ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች የሚካሄዱባቸው የኮንፈረንስ ማዕከላት ያሉባት ከተማ ናት፡፡

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review