የገዳ ሥርዓት እሴቶችን ለዘመናዊ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መጠቀም እንደሚገባ ምሁራን አስገነዘቡ

You are currently viewing የገዳ ሥርዓት እሴቶችን ለዘመናዊ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መጠቀም እንደሚገባ ምሁራን አስገነዘቡ

AMN – ግንቦት 9/ 2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ የሚስተዋለው ያልዳበረ የፖለቲካ ባሕል ሊታከም የሚችለው ገዳን መሰል ደማቅ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን በሥራ ላይ በማዋል እንደሆነ ኤ ኤም ኤን ያነጋገራቸው የዘርፉ ምሁራን ተናገሩ።

የገዳ ሥርዓት እሴቶችን በዘመናዊው የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ፣ በምርጫ ወቅት የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና ለጠንካራ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታም የላቀ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

የገዳ ሥርዓት ያለምንም ጦርነትና ግጭት በየስምንት ዓመቱ የሚከናወነው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የሚካሄድበት ሌላኛው ደማቅ እሴት መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲትይ የስነ- ሰብ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ታደሰ በሪሶ አብራርተዋል፡፡

በሥርዓቱ ውስጥ መሪዎች ጊዜያቸውን ጠብቀው፣ ተመራርቀውና ተሳስመው ሥልጣንን ለተተኪው የሚያስረክቡበት መንገድ መሆኑ በዘመናዊው ፖለቲካ ውስጥ ለሚታዩት እንደ መፈንቅለ መንግሥት እና የምርጫ ማጭበርበሮች ትልቅ መፍትሔ ሊሆን እንደሚችል ፕሮፌሰሩ ለኤ ኤም ኤን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለሺህ ዘመናት የተሻገሩና በዘመናት ሂደት የዳበሩ እልፍ ሀገርበቀል ዕውቀቶችና ሀብቶች ባለቤት መሆኗን የገለጹት ምሁራኑ፣ የገዳ ሥርዓት ለዘመናዊ ዲሞክራሲ የፍልስፍና መነሻ መሆን የሚችል ታላቅ እሴት መሆኑንም አስረድተዋል።

ሥርዓቱ ፍትሐዊ አስተዳደርን የሚያሰፍንና በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሪ የሚመረጥበት ጥብቅ የብቃት መመዘኛ ያለው መሆኑ በተለይም አንድ አባገዳ ከመመረጡ በፊት ለ27 እና ለ28 ዓመታት ያህል በሥነ-ምግባር፣ በአስተዳደር ብቃትና በማኅበራዊ ኃላፊነት አወጣጥ በዝርዝር እንደሚገመገም ተገልጿል።

በተጨማሪም አንድ መሪ በሥልጣን ዘመኑ በአራተኛው ዓመት ላይ በሕዝብ እንደሚገመገም ሌላኛው ምሁር በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት አቶ አሰፋ በዳሶ አስረድተዋል።

ተመራማሪው አክለው ኢትዮጵያ እንዲህ ያሉ ዓለምን ሊያስተምሩ የሚችሉ ሀገርበቀል እሴቶች ቢኖሯትም፣ እነዚህን ከመጠቀም ይልቅ የባህር ማዶ ፖለቲካን መቅዳት ሀገርን አያሌ ዋጋ እንዳስከፈለ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

አቶ አሰፋ በዳሶ እንደሚሉት፣ ደርግም ሆነ ኢሕአዴግ የቀደሙ መሪዎችንና ባለሙያዎችን እንደ አማካሪ በመጠቀም ዕውቀታቸውን ወደ ልማትና ወደ ፖለቲካ መሻሻል ከማሻገር ይልቅ፣ በማግለልና በመግደል የሀገርን ወርቃማ ዘመን እንዳሳጧት ተጠቁሟል።

ምሁራኑ አክለውም የተኮረጀ የፖለቲካ ጉዞ በትውልድ መካከል ልዩነትን በመስበክና ለውጭ ጣልቃ ገብነት በር በመክፈት ዛሬ ድረስ ያልተሻገርነው የታሪክ ዕዳ አስረክቦናል ብለዋል።

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት እየታዩ ያሉ ሀገርበቀል ዕውቀቶችን የመጠቀም ጅማሬዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባና የታመመው የሀገሪቱ ፖለቲካ በገዳ ሥርዓት እሴቶች ሊታከም እንደሚገባ ምሁራኑ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ አሳስበዋል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review