AMN – ግንቦት 09/2018 ዓ.ም
በልደታ ክፍለ ከተማ የተገነባውን የዶሮና የወተት ላም የእንስሳት እርባታ ክላስተር መስሪያ ቦታ ለተጠቃሚዎች የማስተላለፍ መርሃ ግብር ተከናውኗል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ፤ የተገነባው የእንስሳት እርባታ ክላስተር በዘመናዊ የአመራረት ዘዴዎች የተደገፈ መሆኑን ገልጸዋል።
«ግብርና በገጠር ብቻ ሳይሆን በከተማም ጭምር ውጤታማና አምራች መሆን እንደሚቻል በተጨባጭ ያየንበት ነው» ያሉት አቶ ሚሊዮን፣ መሰል ስራዎች በተለይም ለወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው አስገንዝበዋል።

የአዲስ አበባ የከተማ ግብርና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ባዩ ሽጉጤ በበኩላቸው፤ በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ ክላስተሮች ውስጥ የሚከናወኑ የዶሮ እርባታ፣ የወተት ልማትና ሌሎች የእንስሳት ተዋጽኦ ምርት ሥራዎች ለነዋሪዎች ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቁመዋል።
አያይዘውም ክላስተሮቹ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠርና የማህበረሰቡን የኢኮኖሚ ተሳትፎ ለማሳደግ ታስበው የተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የልደታ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ልዕልቲ ግደይ በበኩላቸው፣ የእንስሳት እርባታ ክላስተሩ በተደራጀ መልኩ የዶሮ፣ የወተት እና ሌሎች የግብርና ልማቶችን በአንድ ስፍራ በማካተት የተገነባ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ የአርባታ ስፍራ ለወጣቶችና ለሴቶች ሰፊ የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ፣ የግብርና ምርቶችን በቀጥታ ለህብረተሰቡ የሚያቀርቡበት የመሸጫ ቦታም ጭምር አብሮ የተመቻቸለት መሆኑን ሥራ አስፈጻሚዋ አብራርተዋል።
በእንስሳት እርባታ ክላስተሩ በማህበር በመደራጀት የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች፣ የተሰጣቸውን ሰፊ ዕድል በመጠቀም ተግተው እንደሚሠሩና ራሳቸውንና ሀገራቸውን እንደሚጠቅሙ ለኤ ኤም ኤን በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።
በመሐመድኑር ዓሊ