የአዲስ አበባ ከተማ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ምክንያት በማድረግ የወዳጅነት ስፖርታዊ ውድድር አካሄዱ

You are currently viewing የአዲስ አበባ ከተማ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ምክንያት በማድረግ የወዳጅነት ስፖርታዊ ውድድር አካሄዱ

AMN – ግንቦት 13/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ ለምርጫው የሚፎካከሩ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት በአዲስ ስፖርት ፓርክ ልዩ ልዩ ስፖርታዊ ውድድሮችን አካሂደዋል፡፡

ስፖርታዊ ውድድሩን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እና የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የጋራ ትብብር ያዘጋጁት ነው፡፡

በውድድሩ ላይ የታደሙት የተለያዩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች አንድ በሚያደርጉን ሀገራዊ ጉዳዮቻችን ላይ ያለንን አንድነት አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ምክንያት በማድረግ በካርድ ብቻ በሚል መሪ ሃሳብ የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች አካሂደዋል፡፡

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሊካሄድ በቀናት ብቻ የሚቆጠር ጊዜ ቀርቶታል፡፡

ስፖርት የሠላማዊ ፉክክር መገለጫ እንደመሆኑ መጪው ምርጫም ሠላማዊ የፉክክር መድረክ መሆኑን ለማሳየት የጋራ ስፖርታዊ ውድድሩ መዘጋጀቱን ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ማሩ ጃኔ፣ በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ለመስራት ምቹ መደላድል የፈጠረላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለመጪው 7ኛ ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ ለመስጠት ካርድ የወሰዱ የከተማዋ ነዋሪዎችም ይበጀናል፤ ሀገርንም ወደላቀ ልማት፤ ሠላምና ዕድገት ያሻግራል ለሚሉት ተፎካካሪ ፓርቲ በምርጫው ዕለት ድምጻቸውን እንዲሰጡም የተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አባላት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከድምጽ መስጠት በኋላም የምርጫው ውጤት ሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ የሚመጣውን ውጤት በጸጋ ተቀብሎ ሠላማዊ ትግሉን በላቀ ሁኔታ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉም ተፎካካሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ከ47 ያላነሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት በውድድሩ ተሳትፈዋል፡፡

በምትኩ ተሾመ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review