የበጎነት መንደር ማህበራዊ ትስስርን በማጠናከር ለዜጎች ሁለንተናዊ ድጋፍና የስራ እድል እየፈጠረ ይገኛል

You are currently viewing የበጎነት መንደር ማህበራዊ ትስስርን በማጠናከር ለዜጎች ሁለንተናዊ ድጋፍና የስራ እድል እየፈጠረ ይገኛል

AMN – ግንቦት 13/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረው የበጎነት መንደር ግንባታ የዜጎችን ማህበራዊ ትስስርን በማጠናከር በጎ ፈቃደኝነት እና የመረዳዳት ባህል እንዲጎለብት አድርጓል፡፡

የበጎነት መንደር ግንባታ አላማ ማህበራዊ ትስስርን ለማጠናከር እና የተቸገሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በዘላቂነት ለመደገፍ ታስቦ የተጀመረ መርሐ ግብር ነው።

ዜጎች ሰብዓዊ ክብራቸው ተጠብቆ፣ ክህሎታቸውን አሳድገውና ራሳቸውን ችለው ለሀገራቸው አምራች ዜጋ የሚሆኑበትን ዘላቂና ሁሉን አቀፍ ማዕከል መፍጠር ነው።

ለዚህም የበጎነት መንደር አቅመ ደካማ እናቶችን፣ በመኖሪያ መንደሩ የሚገኙ ነዋሪዎቻችን፣ መጠለያ የሌላቸውን ዜጎች፣ አረጋውያንን እንዲሁም ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች የተጋለጡ ወገኖችን እና ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረገ ነው፡፡

በልደታ፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ገብስ ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ደረጃቸውን የጠበቁ በርካታ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች እና ሱቆች ተገንብተዋል፡፡

እስካሁን የተጠናቀቁት የመኖሪያ ቤቶች ለልማት ተነሺዎች እና የኑሮ ጫና ላለባቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ተላልፈዋል፡፡ በመኖሪያ መንደሩ ለሚገኙ ነዋሪዎች የእንጀራ ፋብሪካን ጨምሮ ልዩ ልዩ የስራ እድልም ተፈጥሯል፡፡

ይሄም ለመኖሪያ ምቹ የሆነ ከባቢ በመፍጠር የዜጎችን የምግብ ዋስትናም ያረጋገጠ ነው፡፡

ከዚህ ባለፈም የበጎነት መንደር በአካባቢው ለሚኖሩ ዜጎች ሁለንተናዊ የህክምና አገልግሎት እና የስነ-ልቦና ድጋፍ ለመስጠትም እገዛ አድርጓል፡፡

በበጎነት መንደር የሕክምና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ የእንጀራ መጋገሪያ ማዕከል፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ የህጻናት መጫዎቻዎች፣ የምገባ ማዕከላት እና መሰል መሰረተ ልማቶችም አብረው እየተገነቡ ይገኛል፡፡

በተለያዩ ማህበራዊ ጫናዎችና በአስቸጋሪ የጎዳና ህይወት ውስጥ ያለፉ ዜጎችን ወደ መደበኛ ህይወት ለመመለስም የስነ-ልቦና ምክርና ድጋፍ የመስጠት ስራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡

በበጎነት መንደር ውስጥ የተለያዩ የሙያ ስልጠና፣ የልብስ ስፌት፣ የፀጉር ስራና፣ የምግብ ዝግጅት ስልጠናዎች የሚሰጡበትን ሂደትን በማመቻቸትም ዜጎች ራሳቸውን እንዲችሉም እየተደረገ ይገኛል፡፡

የበጎነት መንደር የከተማዋ ነዋሪዎች፣ ወጣቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የእርስ በርስ ትስስራቸውን የሚያጠናክሩበት ነው።

መኖሪያ ቤቶች በከተማ አስተዳደሩ እና በበጎ ፍቃደኛ ባለሃብቶች፣ ተቋማት እንዲሁም በህብረተሰብ ተሳትፎ ነው እየተገነቡ የሚገኙት፡፡

ይሄም የቆየውን የኢትዮጵያውያንን የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴት በማሳደግ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ ነው፡፡

ከዚህ ባለፈም በጎዳና ላይ የሚኖሩ ዜጎችን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ የሚቀንስ ሲሆን የከተማዋን ውበት፣ ፅዳት እና አጠቃላይ ማህበራዊ ደህንነትም አሻሽሏል፡፡

የሻምበል ምህረት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review