ህገ-ወጡ የህወሓት ቡድን ሀገርን ለማፍረስ እየፈጸመ ያለውን ክህደት የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው

You are currently viewing ህገ-ወጡ የህወሓት ቡድን ሀገርን ለማፍረስ እየፈጸመ ያለውን ክህደት የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው

AMN – ሐምሌ 9/2018 ዓ.ም

ህገ-ወጡ የህወሓት ቡድን ሀገርን ለማፍረስ እየፈጸመ ያለውን ክህደት የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ሐምሌ 11 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የትግራይ ለሰላም እና ለውጥ ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

ህገ-ወጡ የህወሓት ቡድን ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ተልዕኮ በመቀበል ሀገርን ለማፍረስ እየፈጸመ ያለውን ክህደት የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የፊታችን ቅዳሜ ሐምሌ 11 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡

ምክር ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በትግራይ ክልል ያለው ህገ-ወጥ የህወሓት ቡድን በክልሉ ህዝብ ላይ እያደረሰ ያለው ግፍና መከራ እንደቀጠለ አብራርቷል።

በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት በትግራይ ክልል የተቋቋመውን ጊዜያዊ አስተዳደር በኃይል በመገልበጥ ስልጣንን በህገ-ወጥ መንገድ የያዘው ይህ ቡድን፣ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ተልዕኮ በመቀበል የትግራይ ህዝብ ተመልሶ ወደ ጦርነት አዙሪት እንዲገባ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝም ምክር ቤቱ ገልጿል።

ይህን የህገ-ወጡን ቡድን እኩይ ተግባር ለመቃወም በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች የሚሳተፉበት ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚካሄድ የገለጸው ምክር ቤቱ፣ ሰላም ፈላጊ የሆነው የትግራይ ህዝብ ጦርነት እንደሚበቃው፣ በህገ-ወጡ የህወሓት ቡድን የተጣሰው የፕሪቶሪያ ስምምነት በአስቸኳይ እንዲተገበር እና በክልሉ ዓለም አቀፍ ህግጋትን በጣሰ መልኩ አዋጅ በማውጣት ወጣቶችን ለጦርነት ለመማገድ የሚደረገው የኃይል አፈሳ በአስቸኳይ እንዲቆም የሚሉ ጥያቄዎችና መልዕክቶች በሰልፉ ላይ እንደሚንጸባረቁ አስታውቋል።

ህገ-ወጡ የህወሓት ቡድን ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመሆን አጠቃላይ የአፍሪካ ቀንድን ለማተራመስ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ለቀጣናው ስጋት በመሆኑ፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጠው ምክር ቤቱ ጠይቋል።

በህገ-ወጡ ቡድን ወታደራዊ አፈሳ ምክንያት በርካታ ወጣቶች ትግራይን ጥለው ወደ አዲስ አበባ እየጎረፉ መሆኑን የገለጸው ምክር ቤቱ፣ ሰልፉ እነዚህን ወጣቶች ጨምሮ በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪ የትግራይ ተወላጆች ድምጻቸውን በአንድነት የሚያሰሙበት መድረክ እንደሚሆን አስታውቋል።

በምሩፅ ስብሃት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review