የከተማ አስተዳደሩ ሰው ላይ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል – አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ

You are currently viewing የከተማ አስተዳደሩ ሰው ላይ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል – አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ

AMN – ግንቦት 17/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለዜጎች ቅድሚያ በመስጠት፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖችን በመመገብና በማቋቋም ወደ ሥራ እያስገባ እንደሚገኝ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ እና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ ገለጹ።

ኃላፊው ይህንን ያሉት በተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት ተጠቃሚ የነበሩ 400 የሚሆኑ ዜጎች ከተረጅነት ወደ ሥራ ፈጣሪነት የተሸጋገሩበትን መርሃ ግብር አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት ነው።

አቶ ሚሊዮን፣ ይህ ተግባር የከተማ አስተዳደሩ ሰው ተኮር ለሆኑ ሥራዎች ቅድሚያ ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ማሳያ ነው ብለዋል።

በሽግግር መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ የሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ቆንጅት ደበላ በበኩላቸው፤ የከተማ አስተዳደሩ በተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት ዜጎችን ከመመገብ ባለፈ፣ ከተረጅነት ወደ ሥራ ፈጣሪነት ማሸጋገር ተቀዳሚ ዓላማው መሆኑን ገልጸዋል።

የምገባ ማዕከላቱ የጥገኝነት ማሳያ ሳይሆኑ፣ ዜጎች ራሳቸውን ችለው ወደ ሥራ የሚሰማሩባቸው መሸጋገሪያ ድልድዮች ናቸው ብለዋል።

በዛሬው ዕለት ከተረጅነት ወደ ሥራ ፈጣሪነት ለተሸጋገሩ 400 ተጠቃሚዎች፣ ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችላቸው የመሥሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገላቸው ሲሆን፤ በተጨማሪም መንቀሳቀሻ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ ተበርክቶላቸዋል፡፡

ከተረጅነት ወደ አምራችነት የተሸጋገሩት የማኅበረሰብ ክፍሎች በሰጡት አስተያየት፤ የከተማ አስተዳደሩ እያከናወነ ያለው ዘላቂ ድጋፍ በሕይወታቸው ላይ ትልቅ ለውጥ ማምጣቱን ገልጸው፣ ለተደረገላቸው ድጋፍና እገዛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በንጉሱ በቃሉ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review