የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ የእቃ አስተላላፊነት ዘርፍን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ለማድረግ ውሳኔ አሳለፈ

You are currently viewing የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ የእቃ አስተላላፊነት ዘርፍን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ለማድረግ ውሳኔ አሳለፈ

AMN – ግንቦት 17/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ ባካሄደው ስብሰባ፣ የእቃ አስተላላፊነት ዘርፍን ለውጭ ባለሀብቶች ተሳትፎ ክፍት ለማድረግ ውሳኔ አሳልፏል።

ቀደም ሲል የውጭ ባለሀብቶች በዕቃ አስተላላፊነት የኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ ሊኖራቸው የሚችለው ተሳትፎ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች የቅንጅት ኢንቨስትመንት የተከለለ የነበረ ሲሆን፤ የውጭ ባለሀብቶች የካፒታል የሽርክና ተሳትፎም በ49% ተገድቦ ቆይቷል።

ከዚህም የተነሳ በዘርፉ ላይ የሚፈለገው አዲስ የኢንቨስትመንት ፍሰት ላይ ክፍተት ፈጥሮ የቆየ ሲሆን፣ የቦርዱ ውሳኔ ይህንንና መሰል ችግሮችን የሚቀርፍ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ይህ ውሳኔ በዘርፉ የተሰማሩ ነባር ባለሀብቶችንም ሆነ አዲስ ወደ ዘርፉ ለሚገቡት ባለሀብቶች በሎጂስቲክስ ዘርፉ ላይ ተጨማሪ እምነት እንዲያሳድሩ የሚያግዝ ነው።

በውሳኔው መሠረት ዘርፉን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት መደረጉ ፈጣን፣ ቀልጣፋ እና ዘመናዊ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ለመስጠት፣ ሀገራዊ የሎጂስቲክስ ወጪን ለመቀነስ፣ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማምጣት፣ እንዲሁም የሀገር ውስጥ ተዋናዮች አቅማቸውን አሳድገው ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማድረግ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን እየሠራ ሲሆን፣ ይህ ውሳኔም የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን የኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review