AMN – ግንቦት 20/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ በብዛት ከሚከሰቱ የካንሰር አይነቶች መካከል የአንጀት ካንሰር በአሁኑ ወቅት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስና አሳሳቢ እየሆነ የመጣ ጤና ስጋት ሆኗል።
የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የውስጥ ደዌ፣ የጉበትና የአንጀት ስፔሻሊስት ሐኪም ዶ/ር ሚፍታህ ደሊል ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የአንጀት ካንሰር የሚከሰተው በትልቁ አንጀት ላይ ነው።
በአገሪቱ ከሚገኙ አምስት የካንሰር ሕመምተኞች መካከል አንዱ የአንጀት ካንሰር ተጠቂ መሆኑን የገለጹት ሐኪሙ፤ በሽታው በሴቶች ላይም ከጡት እና ከማህፀን በር ካንሰር ቀጥሎ በከፍተኛ ደረጃ የሚገኝ ዋነኛ የካንሰር አይነት መሆኑን ጥናቶች እንደሚያመለክቱ አብራርተዋል።
ይህ የካንሰር ዓይነት ሲከሰት በሰገራ ላይ የደም ምልክት ማየት፣ ድንገተኛና ከፍተኛ የሆድ ድርቀት ወይም ተቅማጥ ማስተዋልና ያለምንም ግልጽ ምክንያት የሰውነት ክብደት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ዋነኞቹ የበሽታው ምልክቶች መሆናቸውን ዶ/ር ሚፍታህ አስረድተዋል።

በሽታው ምንም እንኳ ትክክለኛ መንስኤው ሙሉ በሙሉ ባይታወቅም፤ የታሸጉና በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችን፣ ቀይ ሥጋና ዘይት የበዛባቸውን ምግቦችን ማዘውተር፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ከመጠን በላይ የሰውነት ውፍረት እና በቤተሰብ ውስጥ የአንጀት ካንሰር ታሪክ መኖር ለበሽታው የመጋለጥ ዕድልን በከፍተኛ ሁኔታ የሚጨምሩ ምክንያቶች ናቸው።
በአንጻሩ ቃጫማ የሆኑ ምግቦችን፣ አትክልትና ፍራፍሬዎችን አዘውትሮ መመገብ በሽታውን ለመከላከል ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ሐኪሙ ጠቁመዋል።

የአንጀት ካንሰር በቆየና በዘገየ ቁጥር የመዳን ዕድሉ በጣም እየቀነሰ የሚመጣ ቢሆንም፣ በሽታው በጊዜ ከተደረሰበት ግን ሙሉ በሙሉ የመዳን ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑን ዶ/ር ሚፍታህ አስገንዝበዋል።
የሕክምና አማራጮቹን በተመለከተም በሽታው ገና ሳይስፋፋ በመጀመሪያው ደረጃ ላይ ከተደረሰበት በኢንዶስኮፒ ብቻ በማከም ሙሉ በሙሉ ማዳን ይቻላል።
ሕመሙ መካከለኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ ደግሞ በቀዶ ሕክምና የተጠቃውን የአንጀት ክፍል ቆርጦ በማውጣት ማከም የሚቻል ሲሆን፤ ካንሰሩ በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋፍቶ በመጨረሻው ደረጃ ላይ በሚገኝበት ወቅት የቀዶ ጥገና፣ የኬሞቴራፒ እና የጨረር ሕክምናዎች በጥምረት እንደሚሰጡ ዶ/ር ሚፍታህ ደሊል በዝርዝር አብራርተዋል።
በበረከት ጌታቸው
See less