AMN-ግንቦት 21/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ ለመስጠት 54 ነጥብ 5 መራጮች ተመዝግበዋል፡፡
ይህንን የዘንድሮውን ምርጫ ከቀደሙት ምርጫዎች ሁሉ ፍጹም የተለየ እና ታሪካዊ ያደረጉት ምክንያቶች እንዳሉም መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
የቁጥሩ በከፍተኛ ደረጃ መጨመር ዋነኛው ምክንያት ዘንድሮ የተጀመረው ዲጂታል የምዝገባ ሥርዓት ነው።
መራጮች በአካል ምርጫ ጣቢያ መሄድ ሳያስፈልጋቸው፣ ባሉበት ሆነው በሞባይል ስልካቸው በምርጫዬ መተግበሪያ አማካኝነት በቀላሉ መመዝገብ እንዲችሉ ተደርጓል፡፡
ይህ አሰራር በተለይም ወጣቱን እና ስራ የሚበዛባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በምርጫው ላይ በንቃት እንዲሳተፍ ትልቅ በር ከፍቷል።
ሌላው የምዝገባ ሥርዓቱ ከብሔራዊ መታወቂያ (ፋይዳ) ጋር መቆራኘቱ ሂደቱን እጅግ ፈጣን እና አስተማማኝ አድርጎታል።
በአንድ በኩል የአንድን ሰው ማንነት በሰከንዶች ውስጥ ለማረጋገጥ ሲረዳ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ድጋሚ ምዝገባን ሙሉ በሙሉ ስለሚያስቀር የሰነድ ማጣራት ሂደቱን አቅልሎታል።
ስለዚህ የቴክኖሎጂ ተደራሽነት መፍጠሩ እና የምዝገባ ሂደቱ ቀላል እና ፈጣን መሆኑ ዜጎች ያለምንም እንግልት መብታቸውን እንዲጠቀሙ ስላደረገ የመራጮች ቁጥር በአስደናቂ ሁኔታ ሊጨምር እንደቻለ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
በአስማረ መኮንን